በድሬዳዋ እና ጅግጅጋ ከተሞች ከ66 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ እና ጅግጅጋ ከተሞች ከ66 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 2/2015 በድሬዳዋ እና ጅግጅጋ ከተሞች ከ66 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።
በድሬዳዋ ጉምሩክ ጽህፈት ቤት ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት እርጥብ ጫት፣ እና ሌሎች የኮንትሮባንድ እቃዎች በሕገወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ ሲሉ በተለያዩ ኬላዎች መያዛቸውን አመልክቷል።
በተመሳሳይ የጅግጅጋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከታህሳስ 25 እስከ 30 2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 12 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው እርጥብ ጫት እና ሌሎች የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን መያዙን ገልጿል።
የጉምሩክ ኮሚሽን በሕግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹ አመራሮች እና ሰራተኞች፣ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አባላት፣የአካባቢው ፖሊሶች እና ሕብረተሰቡ ምስጋናውን አቅርቧል።
የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል የጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ሕብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።