ቀጥታ፡

የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ብሔራዊ የሳይንስ ሙዚየምን መጎብኘታቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 2/2015 ባለፉት ሦስት ወራት የሀገራት መሪዎችንና የአለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎችን ጨምሮ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ብሔራዊ የሳይንስ ሙዚየምን መጎብኘታቸውን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያን የወደፊት ጉዞ መዳረሻ ያመለክታል የተባለለት ብሔራዊ የሳይንስ ሙዚየም ባሳለፍነው መስከረም በአዲስ አበባ ከተማ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ መከፈቱ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርቃቱ ላይ የሳይንስ ሙዚየሙ ህጻናትና ወጣቶች የፈጠራ ሀሳቦችን እንዲለማመዱና እንዲያሳድጉ የሚያስችሉ ማዕከላት እንዳሉት ጠቅሰው ይህም የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት መሰረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል።

May be an image of 13 people, people standing, people sitting and indoor

በብሔራዊ የሳይንስ ሙዚየሙ ወቅታዊ እንቅስቀሴ ዙርያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ተስፋዬ ዘውዴ በሳይንስ ሙዚየሙ እስካሁን ድረስ በቀጠለው ኤግዚቢሽን በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ግኝቶች እየቀረቡ ነው ብለዋል።

በሙዚየሙ በጤና፣ በሮቦቲክ፣ በትምህርት፣ በፋይናንስ፣ በግብርና ፣ በትራንስፖርት፣ በደኅንነትና በሌሎች ዘርፎች መቅረባቸውን ገልጸው ግኝቶቹ ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለአህጉሪቱ ችግርን በራስ አቅም መፍታት እንደሚቻል ማሳያ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስም 20 የሚደርሱ ግኝቶችን በሙዚየሙ ለእይታ ማቅረቡን ያነሱት ኃላፊው በኢንስቲቲዩቱ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የሚደረግላቸው 38 ጀማሪ የግል አልሚዎች፣ ኢትዮ ቴሌኮምና የመረጃ መረብ ደህንነት አስተዳደር ግኝቶቻቸውን ካቀረቡት መካከል እንደሚገኙበት አስታውቀዋል።

የሳይንስ ሙዚየሙ ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ የአለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ተማራማሪዎች፣ ከ18 ሀገራት የተውጣጡ ጋዜጠኞች፣ ተማሪዎችና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሳይንስ ሙዚየሙን ጎብኝተዋል ብለዋል።

May be an image of 6 people, people standing and indoor

በዚህም የሳይንስ ሙዚም ከተመረቀበት መስከረም 24 ቀን 2015 ጀምሮ እስካሁን ድረስ 948 ሺ 919 ሰዎች ጎብኝተውታል ብለዋል።

አቶ ተስፋዬ አክለውም የሳይንስ ሙዚየሙ እንደ ሀገር ከሚሰጠው ብሔራዊ ጥቅም ባለፈ በአህጉሪቱ ለሚገኙ ተመራማሪዎች የሳይንሳዊ ምርምር ውጤቶቻቸውን ለማቅረብ እድል የሚፈጥር ይሆናል ብለዋል።

ለተማሪዎችና ለታዳጊዎች በዘርፉ እንዲሰማሩ መነሳሻ ይሆናል ያሉት አቶ ተስፋዬ በሙዚየሙ ስራዎቻቸውን ያቀረቡ ጀማሪ አልሚዎች ከተቋማትና ግለሰቦች ጋር የስራ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችላቸውም ተናግረዋል።

አሁን ድረስ በቀጠለው ጉብኝት ማንኛውም ሰው ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ ምሽቱ 11 ሰዓት ድረስ መጥቶ የሳይንስ ሙዚየሙን መጎብኘት ይችላልም ሲሉ ገልጸዋል።

May be an image of 5 people, child, people standing and indoor

ሳይንስና ጥበብን በጋራ አጣምሮ በያዘ የኪነ-ህንጻ ንድፍ የተገነባ መሆኑ የተገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሳይንስ ሙዚየም በ6 ነጥብ 78 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ሙዚየሙ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ የሳይንስ እድገት ከፍተኛ አበርክቶ እንደሚኖረው ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም