ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል በ6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች ለሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ከ2 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ድምፅ ሰጪዎች ተመዝግበዋል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 1/2015 በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በ6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች ላይ ለሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ከ2 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ድምፅ ሰጪዎች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት ህዝበ ውሳኔውን ሊያሰናክል የሚችል ምንም አይነት የጸጥታ ችግር አለማጋጠሙንም ቦርዱ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ የሚካሄደውን ሕዝበ ውሣኔ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።

የቦርዱ ሰበሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ 11 የዞን እና ልዩ ወረዳዎች የህዝበ ውሳኔ ጽህፈት ቤቶች ተቋቁመው ምዝገባው እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በኮንሶ ዞን እንዲሁም አሌ እና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች በህዝበ ውሳኔው እንዲሳተፉ ምዝገባ መካሄዱን ጠቅሰው፤ በዚህም 1 ሺህ 727 ድምጽ ሰጪዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በ24 ጣቢያዎች የህግ ጥሰት ተፈጽሞ በመገኘቱ ምዝገባው መሰረዙን ገልጸዋል።

በቀጣይም በእነዚህ ጣቢያዎች አዲስ አስፈጻሚዎች ተመርጠው እስከ ጥር 3 ቀን 2015 ድረስ ምዝገባው እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

በድርጊቱ የተሳተፉ አካላት በህግ እንዲጠየቁ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

ቦርዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሰል ውሳኔዎችን ለማካሄድ በቂ ልምድ እያካበተ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡  

እስካሁን ባለው ሂደትም በአጠቃላይ ከ2 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ድምፅ ሰጪዎች መመዝገባቸውንም ተናግረዋል፡፡

የድምጽ መስጫ ወረቀትን በተመለከተም "ስድስቱ ዞኖች እና አምስቱ ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል መደራጀታቸውን እደግፋለሁ" ለሚለው ህዝበ ውሳኔ ምልክት ነጭ እርግብ መመረጡን፤ "በአንድ ክልል መደራጀታቸውን አልደግፍም" ለሚለው ምልክት ደግሞ ጎጆ ቤት ስለመመረጡ አብራርተዋል፡፡ 

በዚህም የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመት የመራጭ ቁጥርን መሰረት አድርጎ መታዘዙን ተናግረዋል። 

ጥር 29 ቀን 2015 በሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ በታዛቢነት የመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ሀገር በቀል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጀቶች መስፈርቱን አሟልተው እውቅና ማግኘታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ 

በዚህም በአጠቃላይ 5 ሺህ 274 ታዛቢዎች እንደሚሰማሩ ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተውጣጡ 117 ታዛቢዎችና 17 የሰብአዊ መብት ተቆጣጣሪዎች የመራጮች ምዝገባ ሂደትን ለመታዘብ በመስክ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም