ትኩረት በተሰጣቸው የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ተወዳዳሪ የውጭ ኩባንያዎችን ለመሳብ በሚደረገው ጥረት የሚሲዮኖች ሚና ከፍተኛ ነው - የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
ትኩረት በተሰጣቸው የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ተወዳዳሪ የውጭ ኩባንያዎችን ለመሳብ በሚደረገው ጥረት የሚሲዮኖች ሚና ከፍተኛ ነው - የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 1/2015 ቅድሚያ ትኩረት በተሰጣቸው የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ የሚሳተፉ ተወዳዳሪ የውጭ ኩባንያዎችን ለመሳብ በሚደረገው ጥረት የሚሲዮኖች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
በሱሉልታ የአፍሪካ አመራር የልሕቀት ማዕከል ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ለሚሲዮን መሪዎች የሚሰጠው ሥልጠና እንደቀጠለ ነው።
በዛሬው ዕለትም በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ በኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለፃ ተሰጥቷል።
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከትናንት እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን ገፅታ የዳሰሰ ጽሑፍ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ባለፉት አራት ዓመታት ዘረፉን ለማሳደግ የተወሰዱ እርምጃዎችንና የተደረጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በተመለከተም ገለፃ ማድረጋቸው ተገልጿል።
በአራቱ ዓመታት ውስጥ ከአሁን በፊት በመንግስት ቁጥጥር ስር ብቻ ተይዘው የነበሩ ዘርፎች ለግል ኩባንያዎች ክፍት መደረጋቸውን አንስተዋል።
አቶ መላኩ የውጭ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ደረጃ ለመሳብ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን፣ ያጋጠሙ ፈተናዎችና የመፍትሔ አቅጣጫዎችንም አብራርተዋል።
በዚህ ወቅት ሚሲዮኖች በማምረቻው ዘርፍ ብቃት እና አቅም ያላቸው ኩባንያዎችን ወደ አገር ቤት እንዲገቡ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና መጫወት አለባቸው ብለዋል።
ለኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን፣ ያሉ አቅሞችን እና ከመንግስት የቀረቡ ማበረታቻዎችን በተገቢው ደረጃ ማድረስ ከሚሲዮኖች እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።