ቀጥታ፡

በተለየዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ቀጣይነት ባለውና በተደራጀ አግባብ ከዲያስፖራው ጋር ተቀራርበው መስራት አለባቸው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 1 ቀን 2015 በተለየዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ቀጣይነት ባለውና በተደራጀ አግባብ ከዲያስፖራው ጋር ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው ተገለፀ።

በአፍሪካ አመራር የልህቀት ማዕከል ለሚሲዮን መሪዎች፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች እና ለተጠሪ ተቋማት እየተሰጠ ያለው ስልጠና እንደቀጠለ ነው። 

በዛሬው እለትም በአሜሪካ ፍሎሪዳ ዩኒቨርሰቲ የአካዳሚክና ምርምር ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ደረጄ በፈቃዱ በአባይ ወንዝ ዙሪያ ባዘጋጁት ጽሁፍ ላይ ገለፃ አድርገዋል። 

ዶክተር ደረጄ እንደተናገሩት ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች በውጭ አገር በተሰማሩበት የሙያ መስክ ኢትዮጵያን ማገዝ አለባቸው፡፡ 

ለዚህ ደግሞ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ጉዳይ በሚመለከት ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ እንዲደርሳቸው መስራት እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡ 

ከዚህ አኳያ በዓባይ ጉዳይ ላይ የፃፉት መጽሀፍ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማዳበር እንደሚያግዝም ነው ያስረዱት።  

በተለይ በውሃ ሃብት አጠቃቀም ላይ እውቀትና ክህሎት ያላቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በሙያቸው ሊያግዙ እንደሚገባ ተናግረው፤ ለዚህ ደግሞ የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል። 

በመሆኑም በተለየዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ቀጣይነት ባለውና በተደራጀ አግባብ ከዲያስፖራው ጋር ተቀራርበው መስራት አለባቸው ነው ያሉት፡፡ 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ በበኩላቸው ዶክተር ደረጄ በአባይ ወንዝ ላይ ያዘጋጁት መጽሃፍ ዲያስፖራው በወንዙ አጠቃቀም ላይ የተሻለ መረጃ እንዲኖረው እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ 

መጽሀፉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ለሚደረጉ ጥረቶች አጋዥ እንደሚሆን ገልፀው፤ በቀጣይ ሚኒስቴሩ ቀጣይነት ባለው አግባብ ከዲያስፖራው ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም