ስፔናዊው ሮቤርቶ ማርቲኔዝ የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ

17

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 1/2015 የ49 ዓመቱ ስፔናዊ ሮቤርቶ ማርቲኔዝ የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ዛሬ በይፋ ተሾመዋል።

ማርቲኔዝ በኳታር አስተናጋጅነት በተካሄደው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በሩብ ፍጻሜው ፖርቹጋል በሞሮኮ መሸነፏን ተከትሎ ከቡድኑ የተሰናበቱትን ፈርናንዶ ሳንቶስ ተክተዋል።

አሰልጣኙ ለሶስት ዓመት ተኩል የሚቆይ ውል መፈረማቸውንና ውላቸው በ2026 በሚካሄደው 23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ማብቂያ ድረስ እንደሚቆይ ቢቢሲ ዘግቧል።

ሮቤርቶ ማርቲኔዝ በ22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ቤልጂየም ከምድቧ መውደቋን ተከትሎ ከአሰልጣኝነታቸው መሰናበታቸው ይታወቃል።

የፖርቹጋል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማርቲኔዝን በአሰልጣኝነት የመቅጠር ውሳኔ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን “ያልተጠበቀ” ሲሉ በመግለጽ ላይ ናቸው።

የ49 ዓመቱ ስፔናዊ ከዚህ ቀደም ስዋንሲ ሲቲ፣ዊጋን አትሌቲክ እና ኤቨርተንን አሰልጥነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም