ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአልናስር ማሊያ ከሊዮኔል ሜሲ ጋር ሊገናኝ ይችላል

ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአል ናስር ማልያ የሚያደርገው የመጀመሪያ ጨዋታ ከሊዮኔል ሜሲ ጋር ሊያገናኘው ይችላል

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 1/2015 ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሳዑዲ አረቢያው አል ናስር ክለብ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከፈረንሳዩ ክለብ ፓሪሰን ጀርሜን ጋር  ሊያደርግ እንደሚችል ተገለጸ።

ሁለቱ ክለቦች የወዳጅነት ጨዋታቸውን ሐሙስ ጥር 11 2015 ዓ.ም በሪያድ ያደርጋሉ።

ሮናልዶ የሳዑዲ አረቢያውን ክለብ በ173 ሚሊዮን ዩሮ (210 ሚሊዮን ዶላር) የዝውውር ዋጋ መቀላቀሉ የሚታወስ ነው።

ፖርቹጋላዊው ኮከብ ባሳለፍነው ሳምንት ከክለቡ ደጋፊዎች ጋር ትውውቅ አድርጓል።

ክርስቲያኖ ሮናልዶ እስከ አሁን ለአዲሱ ክለቡ ጨዋታ አላደረገም። ለዚህም ምክንያቱ ሮናልዶ በእንግሊዝ የሁለት ጨዋታ ቅጣት ስላለበት ነው።

ተጫዋቹ እ.አ.አ ሚያዚያ 2022 በጉዲሰን ፓርክ ማንችስተር ዩናይትድ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በኤቨርተን 1 ለ 0 ከተሸነፈ በኋላ ወደ መልበሻ ክፍል በሚገባበት የተጋጣሚውን ደጋፊ ስልክ ሰብሯል።

በዚህም ምክንያት በፊፋ ህግ መሰረት የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር በሮናልዶ ላይ የሁለት ጨዋታዎች ቅጣት ጥሎበታል።

ፖርቹጋላዊው ኮከብ በተጣለበት ምክንያት በሳዑዲ ፕሮ ሊግ ሁለት ጨዋታዎች ላይ መሳተፍ አይችልም።

አል ናስር ባሳለፍነው ሳምንት አርብ በሜዳው አል-ታኤን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ ጨዋታውን በስታዲየም በመገኘት ተከታትሏል።

ክለቡ የፊታችን ቅዳሜ ጥር 6 ቀን 2015 ዓ.ም በሊጉ ከአል-ሻባብ ጋር በሚያደርገውም ጨዋታ አይሰለፍም።

የአል ናስር ክለብ አሰልጣኝ ሩዲ ጋርሺያ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ጥር 11 ቀን 2015 ዓ.ም ክለቡ ከፈረንሳዩ ክለብ ፓሪሰን ጀርሜን ጋር በሪያድ በሚያደርገው ጨዋታ የመጀመሪያ ጨዋታውን ሊያደርግ እንደሚችል ለፈረንሳዩ ለ ኪፕ ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።

“የአል ናስር እና አል ሂላል በመቀያየር ከፒኤስጂ የሚያደርጉት የኤግዚቢሽን ጨዋታ ነው። ሮናልዶ የሁለቱን ክለቦች ማልያ ለብሶ ይጫወታል። እንደ መጀመሪያው ጨዋታ ላይቆጠር ይችላል” ሲሉ ገልጸዋል ፈረንሳዊው የ58 ዓመት አሰልጣኝ።

ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሳዑዲ ፕሮ ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታውን የሚያደርገው ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም አል ናስር ከኢቲፋቅ ጋር በሚያከናውኑት ጨዋታ እንደሚሆን ይጠበቃል ሲል የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።

አል ናስር በ12 ጨዋታዎች 29 ነጥብ በመሰብሰብ ሊጉን በመምራት ላይ ይገኛል።

የወዳጅነት ጨዋታው የእግር ኳስ ኮከቦቹን ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ሊዮኔል ሜሲ ዳግም ሊያገናኝ እንደሚችልም ይጠበቃል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም