ቀጥታ፡

የአዕምሮ ህመምን ለከፋ ጉዳት እየዳረገ ያለው የግንዛቤ እጥረት

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 1/2015 የአዕምሮ ሕመም ማለት አንድ ሰው ያለውን አቅም ለመጠቀም፣ በዕለት ተለት ኑሮው የሚያጋጥመውን ውጥረት ለመቋቋም እንዲሁም በሚኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ ፍሬያማ አስተዋፅኦ ለማበርከት የሚያስችለው የስነ-ልቦና ሁኔታ ላይ ሳይሆን ሲቀር እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

መንስዔዎቹም ማህበራዊ፣ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ሊሆኑ እንደሚችሉም መረጃዎቹ ያትታሉ። 

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ከዓለም ሕዝብ 20 በመቶ የሚሆነው በህይወት ዘመኑ አንድ ጊዜ በአዕምሮ ሕመም እና ተያያዥ ጉዳዮች ይሰቃያል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የአዕምሮ ጤናን አስመልክቶ በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ካገኛቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርጓል። 

እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ፤ የአዕምሮ ሕመም አለባቸው የሚባሉ ሰዎችን ፈጥነው ሕክምና ተቋም ቢሄዱ ከሕመሙ የመፈወስ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል። 

በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ለአዕምሮ ጤና እክል የሚጋለጡ ሰዎች ፈጥነው ወደ ሕክምና ስለማይወሰዱ ለውስብስብ ችግሮች ይጋለጣሉ ሲሉም አክለዋል።

በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአዕምሮ ጤና ሕክምና ባለሙያ ዘገየ ዮሐንስ፤ ሕብረተሰቡ ከአዕምሮ ጤና እክል ጋር ተያይዞ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው ይላሉ።

በዋናነትም የጤና እክል የገጠመውን ግለሰብ ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋማት ለመውሰድ በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለው የግንዛቤ ማነስ የታማሚውን ጤና ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ እያደረገው መሆኑንም  እንዲሁ።

በኢትዮጵያ ከቀላል እስከ ከፍተኛ ለሚባሉ የአዕምሮ ጤና እክሎች የሚያጋጥሟቸው ዜጎች ያሉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ድብርትና ጭንቀት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

እነዚህ የአዕምሮ ጤና እክሎች የሚከሰቱባቸው ዜጎችን በፍጥነት ወደ ሕክምና ሥፍራ ለመውሰድ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ለዘብተኝነት እንደሚስተዋልበት አንስተዋል።

የአዕምሮ ጤና እክሎች በሕክምና ሊድኑ የሚችሉ ሲሆን፤ በፍጥነት ሕክምና ካላገኙ ግን ከፍተኛ ለሆነ የአዕምሮ ሕመም ሊያጋልጡ እንደሚችሉ መገንዘብ አስፈላጊ እንደሆነ በመጠቆም። 

የሆስፒታሉ የአዕምሮ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ክብሮም ኃይሌ በበኩላቸው፤ ከአዕምሮ ጤና አኳያ በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ማነስ ታማሚዎች በቂና ፈጣን ሕክምና እንዳያገኙ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በአብዛኛው ታማሚዎች ወደ ሕክምና ሥፍራ የሚመጡት ባህላዊና ሌሎች ቦታዎች ቆይተው ከተዳከሙና የበሽታው ጉዳት ከፍ ካለባቸው በኋላ መሆኑን ይገልጻሉ።

ይህም በሽታውን በፍጥነት ለማዳን ያለውን ዕድል የሚያጠበው ሲሆን በታማሚው ላይ ችግሮችን ጥሎ እንደሚያልፍም አስታውቀዋል።

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አማካሪ አቶ መኮንን አስፋው በበኩላቸው፤ ከአዕምሮ ሕመም አኳያ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የተቀናጀ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ደግሞ በዘርፉ በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚቆዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመታደግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የበሽታውን መከሰት ከሌሎች ጉዳዩች ጋር ከማያያዝ ይልቅ የአዕምሮ ጤና እክል በፍጥነት ሕክምና ካገኘ የሚድን መሆኑን ለማስገንዘብ ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚጠቅምም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም