የጨረራ ቴክኖሎጂን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል የሰው ኃይል አደረጃጀትና የአሰራር ሥርዓት እየተጠናከረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጨረራ ቴክኖሎጂን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል የሰው ኃይል አደረጃጀትና የአሰራር ሥርዓት እየተጠናከረ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 1/2015 የጨረራ ቴክኖሎጂን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል የሰው ኃይል አደረጃጀትና የአሰራር ሥርዓት የማጠናከር ሥራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን ገለፀ።
ጨረራ (ራዲዬሽን) ማለት ኃይል በሞገድ መልክ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በብርሃን ፍጥነት የሚተላለፍ ሲሆን ኃይሉም የራሱ የኤሌክትሪክና የማግኔቲክ መስክ አሉት።
ይህ የጨረራ ቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕክምና፣ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በማዕድንና በግንባታ ዘርፎች ለተለያዩ አገልግሎቶች ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
በኢትዮጵያ ጨረራ በአብዛኛው በህክምናው ዘርፍ ለምርመራና ሕክምና ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ነው የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ጌታቸው የሚናገሩት።
ያም ሆኖ በኢንዱስትሪና በግንባታ ዘርፍ ላይም ጨረራ ጥቅም ላይ የማዋል ጅማሮዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂው ወደ አገር ውስጥ ከገባ ጀምሮ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውልና ትክክለኛውን የአወጋገድ ሥርዓት እንዲከተል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።
በሕግ አፈጻጸም ሂደት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የቅንጅት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ተቋሙ የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን ተብሎ እንደገና መቋቋሙን ገልጸው፤ ጠንካራ የሰው ኃይልና የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም አገሪቱን በዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚያስችላት ነው ያስረዱት።
ኅብረተሰቡ የጨረራ ቴክኖሎጂ ጥቅሞችና አሉታዊ ጎኖቹን በተመለከተ ግንዛቤ እንዲኖረው ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።