ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሞሮኮ አቻው ጋር ሁለተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 1/2015 በአፍሪካ ሀገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና (ቻን) ቅድመ ዝግጅት ሞሮኮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሞሮኮ አቻው ጋር ሁለተኛ የአቋም መለኪያ ጨዋታውን ዛሬ ምሽት 12 ሰአት ላይ ያደርጋል።

ዋልያዎቹ ለቻን ውድድር እያደረጉ ያሉት ዝግጅት ስድስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ የአቋም መለኪያ ጨዋታውን በካዛብላንካ መሐመድ 6ኛ አካዳሚ ዛሬ ከሞሮኮ አቻው ጋር ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ያደርጋል።

ከትናንት በስቲያ የሁለቱ አገራት ብሄራዊ ቡድኖች ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ሞሮኮ 1 ለ 0 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።

በአገር ውስጥ ሊግ የሚገኙ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ሰባተኛው የቻን እግር ኳስ ውድድር በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ከጥር 5 እስከ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቻን ውድድር በምድብ አንድ ከአዘጋጇ አልጄሪያ እንዲሁም ሞዛምቢክ እና ሊቢያ ጋር ተደልድሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም