ኢህአዴግ ችግሮቹን የሚፈቱ ውሳኔዎችን በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው እንደሚያሳልፍ እንጠብቃለን---የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢህአዴግ ችግሮቹን የሚፈቱ ውሳኔዎችን በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው እንደሚያሳልፍ እንጠብቃለን---የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች
መቀሌ መስከረም 22/2011 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር/ኢህአዴግ ያጋጠሙትን ችግሮች የሚፈታባቸውን ውሳኔዎች በ11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤው ያሳልፋል ብለው እንደሚጠብቁ ኢዜአ ያናገራቸው የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። በመቀሌ ከተማ የሀውልት ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ መሃሪ በየነ በሰጡት አስተያየት፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች በትግል ወቅት መስዋዕትነት የከፈሉት ለዜጎች ሰላም፣ ፍትሃዊ የሀብት ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት መረጋገጥ ነው፡፡ በቀጣይ ከኢህአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የዜጎችን ፍትሃዊ የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን እንደሚጠብቁ የተናገሩት አቶ መሃሪ ለዚሁ ተግባራዊነትም እህት ድርጅቶች የጋራ አቋም ይዘው እንዲወጡ ይጠብቃሉ። በመቀሌ ከተማ የቀዳማይ ወያኔ ነዋሪ የሆነችው ወጣት ሳራ ዮሃንስ በበኩሏ 11ኛው “የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ልዩነትን የሚያጠብ በመሆን እንደሚጠናቀቅ እምነት አለኝ” ብላለች፡፡ በመቀሌ ከተማ የሰሜን ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ገብረመድህን አለማየሁ በበኩላቸው በጉባኤው ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን የሚሸራርፉ ተግባራት የሚወገዱበትና ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጡ ተጨማሪ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ ነዋሪዎቹ በጉባኤው የሀገርንና የህዝብን ጥቅም ለማረጋገጥ የሚሰሩና በውጤት የሚለኩ አባላት ወደ አመራርነት ይመጣሉ የሚል ተስፋ እንዳለቸው ገልጸዋል፡፡ 11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ከመስከረም 23 እስከ መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ.ም በሃዋሳ ከተማ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡