ማንችስተር ሲቲ እና ቼልሲ ከሶስት ቀናት በኋላ ዳግም በኤፍኤ ካፕ የሶስተኛ ዙር ጨዋታ ተገናኝተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ማንችስተር ሲቲ እና ቼልሲ ከሶስት ቀናት በኋላ ዳግም በኤፍኤ ካፕ የሶስተኛ ዙር ጨዋታ ተገናኝተዋል

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ታህሳስ 30/2015 በኤፍኤ ካፕ የሶስተኛ ቀን ውሎ ማንችስተር ሲቲ ከቼልሲ ዛሬ ከምሽቱ 1 ሰአት ከ30 በኢትሃድ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
ሁለቱ ክለቦች ከሶስት ቀናት በፊት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተጫውተው ነበር፤ዛሬ ደግሞ በኤፍኤ ካፕ የሶስተኛ ዙር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ማንችስተር ሲቲ እና ቼልሲ በኤፍኤ ካፕ ሲገናኙ የዛሬውን ጨምሮ ለስምንተኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች ማንችስተር ሲቲ 4 እንዲሁም ቼልሲ 3 ጊዜ አሸንፈዋል።

ሁለቱ ክለቦች ለመጨረሻ ጊዜ በኤፍኤ ካፕ የተገናኙት እ.አ.አ በ2021 ሲሆን ቼልሲ በግማሽ ፍጻሜው ማንችስተር ሲቲን በሀኪም ዚዬች ጎል 1 ለ 0 በማሸነፍ ለፍጻሜው አልፏል።
ቼልሲ የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን 8 እንዲሁም ማንችስተር ሲቲ 6 ጊዜ አንስተዋል።
ሁለቱ ክለቦች ባሳለፍነው ሐሙስ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት መርሐግብር በስታምፎርድ ብሪጅ ተገናኝተው ማንችስተር ሲቲ ሪያድ ማህሬዝ ባስቆጠራት ግብ 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወቃል።
የ35 ዓመቱ ሮበርት ጆንስ የሁለቱን ክለቦች የኤፍኤ ካፕ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራሉ።
ትናንት በተደረጉ የኤፍኤ ካፕ ጨዋታዎች የአምናው የውድድሩ አሸናፊ ሊቨርፑል ከዎልቨርሀምፕተን ዎንድረርስ ጋር ያደረገው ጨዋታ ሁለት አቻ ተጠናቋል። ሁለቱ ክለቦች በቀጣይ የመልስ ጨዋታቸውን በዎልቭስ ሜዳ ያደርጋሉ።
ቶተንሃም ሆትስፐር ፖርትስማውዝን እንዲሁም ሌይስተር ሲቲ ጂሊንግሃምን በተመሳሳይ 1 ለ 0 በማሸነፍ ወደ አራተኛ ዙር አልፈዋል።
ኖርዊች ሲቲ ከብላክበርን ሮቨርስ፣ አስቶን ቪላ ከስቲቪኔጅ እና ካርዲፍ ሲቲ ከሊድስ ዩናይትድ ዛሬ ከሚደረጉ የኤፍኤ ካፕ ጨዋታዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ኤፍኤ ካፕ እ.አ.አ በ1871 የተጀመረ አንጋፋ የክለቦች የእግር ኳስ ውድድር ነው።
በሌላ በኩል በስፔን ላ ሊጋ 16ኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬ ምሽት 5 ሰአት በሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም አትሌቲኮ ማድሪድ ከባርሴሎና የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ባርሴሎና በ38 ነጥብ የሊጉ መሪ ነው። አትሌቲኮ ማድሪድ በ27 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ክለቦች በባለፉት አምስት ተከታታይ የላ ሊጋ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው አትሌቲኮ ማድሪድ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ባርሴሎና ያሸነፈው አንዴ ብቻ ነው።
ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።
ትናንት በላ ሊጋው ሪያል ማድሪድ በቪያሪያል 2 ለ 1 መሸነፉን ተከትሎ ባርሴሎና ዛሬ ካሸነፈ ከነጮቹ ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ሶስት ከፍ ማድረግ ይችላል።
በጣልያን ሴሪ አ የ17ኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬም ቀጥሎ ሲውል ከምሽቱ 2 ሰአት ሳምፕዶሪያ በሉዊጂ ፌራሪስ ስታዲየም የሊጉን መሪ ናፖሊ ያስተናግዳል።
በሳን ሲሮ ስታዲየም ከምሽቱ 4 ሰአት ከ45 ኤሲ ሚላን ከሮማ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ሳለረንቲና ከቶሪኖ፣ ስፔዚያ ከሊቼ እና ላዚዮ ከኢምፖሊ ሌሎች ዛሬ የሚደረጉ የጣልያን ሴሪ አ ጨዋታዎች ናቸው።
ትናንት ጁቬንቱስ በሜዳው ዩዲኒዜን አስተናግዶ በዳኒሎ ግብ 1 ለ 0 አሸንፏል።