አማኑኤል ኢሳያስ ኢንተርናሽናል የቮሊቦል ኢንስትራክተር ደረጃን አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
አማኑኤል ኢሳያስ ኢንተርናሽናል የቮሊቦል ኢንስትራክተር ደረጃን አገኘ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 30/2015 ዓለም አቀፉ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ለአማኑኤል ኢሳያስ ኢንተርናሽናል የቮሊቦል ኢንስትራክተርነት ደረጃን ሰጠ።
አማኑኤል በቮሊቦል ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተርነትን ያገኘ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ሆኗል።
“በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቂት ሰዎች ብቻ ሊያገኙት የሚችሉትን” የአሰልጣኞች አሰልጣኝ/ International Instructor/ ደረጃን አማኑኤል ኢሳያስ ከዓለም አቀፉ ቪሊቦል ፌዴሬሽን/FIVB/ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ይህም ከአንጋፋው ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር አለማየሁ ሸዋታጠቅ ቀጥሎ ሁለተኛው ኢትዮጵያውያዊ መሆን እንዳስቻለው ገልጿል።
አማኑኤል በአሁኑ ሰዓት ሶስተኛ ደረጃ /3rd level/ የቮሊቦል አሰልጣኝነት ሰርተፍኬት ያለው ብቸኛ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።
አማኑኤል ኢሳያስ ቮሊቦልን በተጫዋችነት በክለብ ደረጃ በኢትዮጵያ ቡና ክለብ በ1980 ዓ.ም ጀምሯል።
የኢትዮጵያ ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድንንም ለሶስት ዓመት ያህል አገልግሏል።
የተጫዋችነት ዘመኑ በሀገር ብቻ የተገደበ አልነበረም ወደ ታንዛኒያ ተጉዞ ለታንዛኒያው ቲፐር ክለብ ለአምስት ዓመታት በፕሮፌሽናልነት ተጫውቷል።
ወደ አሰልጣኝነቱም ከገባ በኋላ የተለያዩ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠናዎችን በአገር አቀፍ ደረጃ ሰጥቷል።
በታንዛኒያ ቆይታውም የታንዛኒያውን ቲፐር እና ሜትሮ ክለቦች እንዲሁም የታንዛኒያ ብሔራዊ ቮሊቦል ቡድን አሰልጥኗል።
አማኑኤል ከታንዛኒያ መልስ በኢትዮጵያ ሙገር ሲሚንቶ እና ወላይታ ዲቻን አሰልጥኗል።
ከወላይታ ዲቻ ጋር ሁለት ጊዜ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን መሆን ችሏል።
በአሁኑ ሰዓትም ወላይታ ዲቻን በዋና አሰልጣኝነት እየመራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።
አሰልጣኝ አማኑኤል በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጡ ከደረጃ 1 እስከ 3 ያሉ ስልጠናዎችን ወስዶ ያጠናቀቀ ሲሆን በተጨማሪም የተለያዩ ስፔሻላይዜሽን ስልጠናዎች/ሴሚናሮች/ ተከታትሏል።