ቀጥታ፡

ለሀገር ሉአላዊነትና ደህንነት ሲባል የመከላከያ ኃይላችንን ከምንጊዜውም በላይ ለማጠናከር እየተሰራ ነው- የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ሀዋሳ (ኢዜአ) ታህሳስ 29/2015 ለሀገር ሉአላዊነትና ደህንነት ሲባል የመከላከያ ኃይላችንን ከምንጊዜውም በላይ ለማጠናከር እየተሰራ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

በብላቴ የሚገኘው የኮማንዶ እና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል የኮማንዶ ሰልጣኞችን ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሀገሪቱ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ተነጋግሮ ሰላም ማውረድ ትክክለኛና ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ሀገሪቱ ወደ ሰላም ሽግግር ላይ መሆኗን አመልክተው የጀመርነውን የሰላም ጥረታችንን ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት እንንቀሳቀሳለን ብለዋል።

ከዚህ በተፃራሪ ለሚቆሙ ኃይሎች መንገድ አንሰጥም ሲሉም ገልጸዋል።

ለሀገር ሉአላዊነትና ደህንነት ሲባል የመከላከያ ኃይላችንን ከምንጊዜውም በላይ ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኮማንዶና አየር ኃይላችን መላው ሰራዊታችን የሚተማመንበት ጠንካራ ክንዳችን ነው ያሉት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፤ ይህንን ሀይል በላቀ ደረጃ ለመደገፍ፣ ለማስፋትና ለመገንባት ዝግጁነት እንዳለ አረጋግጠዋል።

የዕቱ ተመራቂ ኮማንዶዎችም የዚሁ እንቅስቃሴ አካል መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሠራዊቱ በተሟላ ቁመና ላይ ተገኝቶ ሀገሪቱን ከማናቸውም ጥቃት ለመከላከል ሁል ጊዜ መታጠቅ፣ መዘጋጀትና መሰልጠን እንዳለበት አመላክተዋል።

ብቃታችንን በየጊዜው እያሳደግን በመሄድ ምርጥ የአየር ወለድና ኮማንዶ ኃይል ሆነን ሀገራችንን ለመጠበቅ እንድንችል ታስቦ የተደረገ ስልጠና መሆኑንም ገልጸዋል።

በመከላከያ ሚኒስቴር የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታ በበኩላቸው፤ በእዙ ስር የሚገኘው ማሰልጠኛ ማዕከሉ ሀገራችንንና ሰራዊቱን በሚመጥን ደረጃ ስልጠናዎችን ከዕለት ወደ ዕለት እያዘመነ ይገኛል ብለዋል።

በተለይ ጠንካራ ተዋጊ ኮማንዶ፣ አየር ወለድ፣ ልዩ ኃይል እና ፀረ ሽብር ኃይሎችን አሰልጥነን ማብቃታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም አሰታውቀዋል።

የዕለቱ  ተመራቂዎችም ወደ ኮማንዶና አየር ወለድ እዝ እና ሪፓብሊካን ጥበቃ ኃይሎች በመቀላቀል አኩሪ ገድል ማስመዝገብ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

ተመራቂዎቹ ቀደም ሲል ከተለያዩ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች መደበኛ የእግረኛ ስልጠናዎችን በተሻለ ውጤት፣ ዲሲፕሊንና ብቃት ተመርቀው የኮማንዶ ኮርስ እንዲወስዱ የተመረጡ ናቸው ያሉት ደግሞ የማዕከሉ አዛዥ ኮሎኔል ቦጃ አጋ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ማዕከሉ አደረጃጀቱን በማሻሻልና በማስፋት ጠንካራ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በመሆን ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከምርቃቱ በተጓዳኝ የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ በብላቴ ኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል አቅራቢያ ለሚኖሩ 120 አቅመ ደካሞች የዓይነት ድጋፍ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም