ቀጥታ፡

የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ጠየቁ

አዲስ አበባ መስከረም 22/2011 የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ድምፃቸውን በጋራ አሰሙ። በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው 73ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው አገራቱ ማዕቀቡ እንዲነሳ የጠየቁት። የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ኢሴ አዋድ የአፍሪካ ቀንድ አገራት መሪዎች በመሀከላቸው ያለውን የረዥም ዓመት ግንኙነት፣ የኢኮኖሚና የጋራ ትብብር የላቀ ደረጃ ለማድረስ አጠናክረው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል። በዚህም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የተጣለውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ ማንሳቱ የጋራ ጥቅምን ለማስጠበቅ እንዲሁም ለቀጣናው ኢኮኖሚያዊ እድገት ሚና እንዳለው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎች በሁለቱ አገራት መካከል ሰላም ፈጥረዋል። የኤርትራ እና ጅቡቲ መሪዎችም ረጅም ዓመታት ካስቆጠረ አለመግባባት በኋላ ወደ ሰላም ተሸጋግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በጉባኤው ላይ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሀከል ከ20 ዓመታት በላይ የነበረው አለመግባባት ተወግዶ የሰላም ምዕራፍ መጀመሩን ገልጸው፣ ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውን ወደ ቀድሞው ወዳጅነት ለመመለስ እየሰሩ ነው ብለዋል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፈቂ ማህመት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሀከል የመጣው ሰላም አፍሪካውያን ለችግሮቻቸው መፍትሄ ፈጣሪ የመሆናቸው ማሳያ መሆኑን ገልጸው ለሌሎች አገራት ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል። የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኤርትራ የሶስትዮሽ ጉባኤ ማካሄዳቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የጣለው ማእቀብ መነሳት በአፍሪካ ቀንድ የሚታየውን ለውጥ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የሚከናወን፤ ጊዜውን የጠበቀ እና ተገቢ እንደሚሆን መናገራቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም