''ከጉባዔው ለህዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ ውሳኔዎችን እንጠብቃለን'' - የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
''ከጉባዔው ለህዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ ውሳኔዎችን እንጠብቃለን'' - የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች
ሐዋሳ መስከረም 22/2011 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ) ከነገ ጀምሮ በሐዋሳ በሚያካሂደው ድርጅታዊ ጉባዔ የህዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚመልሱ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ብለው እንደሚጠብቁ ለኢ ዜ አ አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለፁ። በአገሪቱ የሚታዩ ግጭቶችና ሌሎች ችግሮችም በጉባዔው መፍትሄ ያገኛሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል። ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ከተማ ዶባ ጉባዔው ለህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተለይም ደግሞ ለወጣቶች ሥራ አጥነት ችግሮች መፍትሄ የሚሆኑ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ እጠብቃለሁ ብለዋል። "አሁን ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ግጭቶችና የፀጥታ ችግሮች ይስተዋላሉ" ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ ለወቅታዊ አገራዊ ችግሮች መፍትሄ የሚሆኑ ውሳኔዎችን ያሳልፋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። የግንባሩ አባል አራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ነባር አመራሮቻቸውን በአዲስ እየተኩ በመሆናቸው አገራዊ ለውጡን የሚመሩ ወጣትና ምሁራን ወደፊት ይወጣሉ ብለው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል፡፡ "የኢህአዴግ ድርጅቶች አመራሮቻቸውን በአዳዲስ ወጣቶች እየቀየሩ በመሆናቸው በጉባዔው ተመሳሳይ ለውጥ እንጠብቃለን" ያለው ደግሞ ወጣት አረጋ አዳነ ነው፡፡ "አገሪቱን የመምራት ዕድል የሚያገኙ ወጣት አመራሮችም ወጣቱን ከሥራ አጥነት ለማላቀቅ የሚተጉ ይሆናሉ የሚል እምነት አለኝ" ብሏል። ከጉባዔው በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች ምላሽ የሚሰጡ ውሳኔዎችን እንደሚጠብቅም ወጣት አረጋ ገልጻል። "ሰላም ከሁሉም ነገር ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ ጉባዔው በሰላም ጉዳይ ጥልቅ ውሳኔ ያሳልፋል የሚል እምነት አለኝ " ያለው ደግሞ ወጣት ጌታነህ በየነ ነው። "ወጣቱ ወደ አላስፈላጊ ድርጊት እንዲገባ እያስገደደው ያለው ለመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቹ ምላሽ ማጣቱ ነው" ያለው አስተያየት ሰጪ፣ ከጉባዔው መፍትሄ እንደሚጠብቅ ተናግሯል። ወጣቱ ከተዘዋዋሪ ፈንድ ተጠቃሚ የሚሆንበት ውሳኔ በጉባዔው ይተላለፋል የሚል እምነት እንዳለውም ገልጿል። "ከጉባዔው የአገሪቱን ሰላምና እድገት ለማፋጠን የሚረዱ ውሳኔዎችን እጠብቃለሁ" ያሉት ወይዘሮ እመቤት ገረመው ዘረኝነትና የዜጎችን መፈናቀልን የሚያስቀሩ ሀሳቦች በጉባዔው ይነሳሉ ብዬ እጠብቃለሁ ብለዋል። በአመራር ደረጃ እየተደረገ ያለው መተካካት ተገቢ እንደሆነ የገለጹት ወይዘሮ እመቤት፣ ወደ አመራር የሚመጡ ሴቶች ቁጥርም ያድጋል ብለው ይጠብቃሉ። ወይዘሮ ብሩክታይት ቅጣው የተባሉ አስተያየት ሰጭ ኢትዮጵያ የሃይማኖትና የመቻቻል መገለጫ መሆኗን አስታውሰው፣"ይሁን እንጂ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አገሪቱ መልካም ገፅታዋ እየተሸረሸረ መጥቷ" ብለዋል። ጉባዔው ይህንን በማገናዘብ በወቅታዊው የአገሪቱ ሁኔታ ላይ ውሳኔዎች ያሳልፋል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።