ቀጥታ፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲስ የሰራተኛ ድልድል ያደርጋል

አዲስ አበባ መስከረም 22/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተጣለበትን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት የሚያስችለው አዲስ የሰራተኛ ድልድል እንደሚያካሂድ አስታወቀ። ድልድሉ የሚካሄደው በዋናው መስሪያ ቤትና በ58 ሚሲዮኖች እንደሆነ ታውቋል። ሚኒስቴሩ ድልድሉን የሚያደርገው አገሪቱ ከምትገኝበት ውስጣዊ እና ውጫዊ ሁኔታ በመነሳት ውጤታማ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ስራ ለማከናወን መሆኑን አስታውቋል። ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር የተሳለጠ ግንኙነት፣ የሰመረ የመረጃ ፍሰትና ወጥነት ያለው ቅንጅታዊ አሰራርና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖረው ለማድረግም ድልድሉ አስፈልጓል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያዘጋጀው አዲስ ተቋማዊ መዋቅር በጠቅላይ ሚኒስትሩ በመፅደቁ የዲፕሎማቶች ዳግም ድልድል ይከናወናል፡፡ ድልድሉ ብቃትና ክህሎት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ሚኒስቴሩ አመልክቷል። እጅግ ፈጣን በሆነ መልኩ እየተለዋወጠ የሚገኘውን ክልላዊ፣ አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ሁኔታ ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስራ እየጨመረ በመምጣቱ ኃላፊነቱን በበቂ ሁኔታ ለመወጣት የመዋቅር ማሻሻያና አዲስ የሰራተኛ ድልድል አስፈላጊ ሆኗል፡፡ የድልድሉ መመሪያ ትናንት የፀደቀ ሲሆን ምደባውን ለማካሄድ ሰባት የማኔጅመንት አባላትና የሰራተኛ ተወካዮችን የያዘ ኮሚቴ መቋቋሙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም