በሰሜን ንፍቅ ክበብ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የእረፍትና የበዓላት ጊዜያቸውን አገር ቤት እንዲያሳልፉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ንፍቅ ክበብ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የእረፍትና የበዓላት ጊዜያቸውን አገር ቤት እንዲያሳልፉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ታህሳስ 29/2015 /ኢዜአ/ በሰሜን ንፍቅ ክበብ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የእረፍትና የበዓላት ጊዜያቸውን አገር ቤት እንዲያሳልፉ በተለያዩ አገራት ኢትዮጵያን የወከሉ አምባሳደሮች ጥሪ አቀረቡ።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፤ በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ እና በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለስ የገናን በዓል በኢትዮጵያ እያሳለፉ ነው።
የአገር ናፍቆት የሚታወቀው በውጭ ሲኖሩ እንደሆነ የገለጹት አምባሳደሮቹ፤ በዓላትን በአገር ቤት ማክበር ልዩ ስሜት እንዳለው ገልጸዋል።
በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ተቀያያሪና አስቸጋሪ የአየር ፀባይ እንዳለ ጠቅሰው ከበዓላት ሁነቶች ባሻገር በኢትዮጵያ ምቹ የአየር ፀባይ መኖሩ በርካቶችን የሚስብ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዚህም ዳያስፖራው ማኅበረሰብ ቤተሰብን እየያዘ በባህል፣ በታሪክና በተፈጥሯዊ የመስህብ ሀብቶች የታደለችዋን ኢትዮጵያ እንዲጎበኙ ጠይቀዋል።
በተለይም አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች መገንባታቸውን አስታውሰው፤ ከጥምቀትና ሌሎች ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሁነቶች ባሻገር ኢትዮጵያን መጎብኘት ተመራጩ ጊዜ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ባለፈው ዓመት ታላቁ ጉዞ ወደ አገር ቤት' መርሃ- ግብር በርካታ የዳያስፖራ አባላት ወደ አገር ቤት መምጣታቸውን አስታውሰው፤ ይህን ጉዞ በየዓመቱ እንደ ባህል ሊወስዱት ይገባል ነው ያሉት።
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በችግር ላይ መቆየቷን አስታውሰው፤ አሁን ነገሮች ሁሉ ወደ ሰላማዊ መልክ እየያዙ በመምጣታቸው፤ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ- ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት እንዲመጡም ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌትና የታሪክ ባለቤት መሆኗን የጠቆሙት አምባሳደሮቹ፤ ከኢትዮጵያዊያን ባለፈ ሌሎች ጥቁር ሕዝቦች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙም እንደሚሰሩ ተናግረዋል።