ቀጥታ፡

ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን ባህላዊ እሴቶች በመጠቀም ተልዕኳቸውን ሊወጡ ይገባል

አዲስ አበባ ታህሳስ 29/2015 /ኢዜአ/ ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን ባሕላዊ እሴቶች በመጠቀም ተልዕኳቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ በሥልጠና ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ አምሳደሮች የገናን በዓል ምክያት በማድረግ የስፖርት ውድድር ዛሬ አካሂደዋል።

"ባህላችን የዲፕሎማሲያችን መሰረት ነው" በሚል መሪ ሃሳብ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በጋራ በተዘጋጀው በዚህ ውድድር መረብ ኳስ፣ እግርኳስ፣ ገና ጨዋታ፣ የጠረጴዛ ቴኒ፣ ገበጣና የገመድ ጉተታ ጨዋታዎች ተደርገዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በዚህ ወቅት እንዳሉት ባህልና ስፖርትን በተቀናጀና በተሳሰረ አግባብ ለዲፕሎማሲ ዓላማ መጠቀም ይገባል።

ጤናማና ለበለፀገ ማኅበረሰብ ለመገንባት እንቅስቃሴን የሕይወት ቀመር እንዲሁም ስፖርትን ዘወትር የሚከናወን ተግባር ማድረግ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያን የወከሉ ዲፕሎማቶችም ባህልን ለውጤታማ ዲፕሎማሲ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳም ዲፕሎማቶች በየሚሰሩባቸው አገራት የአገራቸውን ባህልና ስፖርታዊ እሴቶች ማንፀባረቅ እንዳለባቸው ጠይቀዋል።

ባህል ለአገራት የእርስ በእርስ ትስስርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ወሳኝ በመሆኑ የኢትዮጵያን የፈጠራ ሥራዎችና ባህሎች አምባሳደሮቹ እንዲያስተዋውቁ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም