የኢዜአ አመራርና ሠራተኞች ለሰሊሆም የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የገና በዓል መዋያ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢዜአ አመራርና ሠራተኞች ለሰሊሆም የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የገና በዓል መዋያ ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 28/2015 የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ አመራርና ሠራተኞች ለሰሊሆም የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የበዓል መዋያ ድጋፍ አደረጉ።
የሰሊሆም የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ሚኪያስ ለገሰ በተባለ ወጣት ነው ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት የተመሰረተው።
ማዕከሉ አሁን ላይ ከ180 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች እርዳታ የሚሰጥ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ የአዕምሮ ሕሙማን ናቸው።
ማዕከሉ አረጋውያን፣ ህፃናት፣ ሴቶችና በአስቸጋሪ የጎዳና ሕይወት ውስጥ የነበሩ ሰዎችን አሰባስቦ ምግብ፣ መጠለያና የጤና አገልግሎቶች እንዲያገኙ ያደርጋል።
ድርጅቱ የራሱ የሆነ ገቢ የሌለውና በኅብረተሰቡ ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ሲሆን እስካሁን ወደ ማዕከሉ መጥተው ሕክምና የተደረገላቸው 34 ሰዎች ድነው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራርና ሠራተኞችም ይህንኑ ሰብዓዊ ተግባር እያከናወነ ላለው ማዕከል የገና በዓል መዋያ ድጋፍ አድርገዋል።
የኢዜአ የሕዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ዳይሬክተር ዮሐንስ ወንዲራድ፤ የአሁኑ ድጋፍ የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች በዓሉን ከተቸገሩ ወገኖች ጋር በጋራ ማክበር ይገባናል ብለው የገና በዓል መዋያ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
በቀጣይም የሰሊሆም የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልን ለመደገፍ የተቻለውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን ሲሉ ተናግረዋል።
የሰሊሆም የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሚኪያስ ለገሰ በበኩላቸው ለተደረገው የበዓል ድጋፍ ምስጋና ቸረው የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
በተለይ ወደ እንጦጦ ፓርክ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያን የሰሊሆም የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልን በዚያው እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።