ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ያስገነባቸውን የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶች አስረከበ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 28/2015 የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በወረዳ 5 በአዲስ መልኩ ያስገነባቸውን አምስት የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶችን አስረከበ።

አገልግሎቱ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግም የበግ፣ የዘይትና የዱቄት ስጦታም አበርክቷል።

በአዲስ መልክ የተገነቡት መኖሪያ ቤቶች በወረዳው ረዳት የሌላቸውና በዝቅትኛ የኑሮ ደረጀ ላይ ለሚገኙ አምስት አባወራና እማወራዎች ለመደገፍ ታስቦ የተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ፤ በአዲስ መልክ የተገነቡት መኖሪያ ቤቶች 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጥቷባቸዋል ብለዋል።

አገልግሎቱ በቀጣይም ከወረዳው ጋር በመቀናጀት ሰው ተኮር በሆኑ የልማት ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ዶክተር አብዱልቃድር አረጋግጠዋል።

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የዴሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽኅፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አበራ መኖሪያ ቤቶቹ ሙሉ በሙሉ ፈርሰው በአዲስ መልክ መገንባታቸውን ገልጸዋል።

ይህም አቅመ ደካሞቹን የተሻለ ቤት ውስጥ እንዲኖሩ በማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

ቤታቸው የታደሰላቸው አቶ ተፈሪ ቱሉና ወይዘሮ ጥሩወርቅ ፈለቀ በአዲስ መልክ የተገነባላቸው የመኖሪያ ቤት ተጠነናቆ ዛሬ በመረከባቸው እንደተደሰቱ ገልጸዋል።

ጎን ለጎንም ተቋሙ ያበረከተላቸው የገና በዓል መዋያ ስጦታም በዓሉን ሳይቸገሩ እንዲውሉ እንደሚያስችላቸው ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም