የሠላም ሥምምነቱ እንዲጸና ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የኃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
የሠላም ሥምምነቱ እንዲጸና ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የኃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 28/2015 በመንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሠላም ሥምምነት እንዲጸና ባለድርሻ አካለት የድርሻቸውን አንዲወጡ የኃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያንና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ-ክርስቲያናት የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን፤ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በመንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሠላም ሥምምነት እንዲጸና ሁሉም አካላት በኃላፊነት አንዲሰሩ የኃይማኖት አባቶቹ መክረዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በፖለቲካ ኃይሎች የተጀመረው የሠላም ሥምምነት እንዳይደናቀፍ ሁሉም አካል በኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብለዋል።
''ኢየሱስ ክርስቶስ በልደቱ ከሰማያት ወርዶ ከሰው ልጆች ጋር እርቅ በማድረጉ ዓለምን አድኗል፤ ይሕ የፈጣሪ ተግባር በእርቅና በሰላም የማይፈታ ጉዳይ እንደሌለ ለሰው ልጆች የሚያመላክት ነው'' ሲሉም የሠላምን አስፈላጊነት አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው፤ ለአገር ሰላምና ለሕዝቦች ደኅንነት ሲባል በሰላም ሥምምነቱ የተገባውን ቃል በማክበር ረገድ ሁሉም አካላት ተገዢ መሆን አለባቸው ብለዋል።
እስካሁን ባለው ሂደት በሰላም ሥምምነቱ የተገባውን ቃል ለመፈፀም እየተደረገ ያለው ጥረት እንዳስደሰታቸው ገልጸው ይህም ለመላው ሕዝብ ዘላቂ ሰላም ያስገኛል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀኃፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ በበኩላቸው በአገሪቱ የተጀመረው የእርቅና የሰላም መንገድ የሁሉንም ተስፋ ያለመለመ ነው ብለዋል።
''ይህ መልካም ጅማሬ በመላው አገሪቱ እንዲስፋፋና እውነተኛ ሰላም እንዲረጋገጥ ሁሉን ቻይ በሆነው አምላካችን ፊት በጾምና በፀሎት አብዝተን እንቅረብ'' በማለት አሳስበዋል።
ኅዝቡም በመተባበርና በመተጋገዝ መንፈስ ለሰላም ሥምምነቱ ተግባራዊነት የበኩሉን እንዲወጣ የቤተ-ክርስቲያኗ የሃይማኖት አባቶች በትኩረት እንደሚሰሩ ነው ያረጋገጡት።