በከተሞች የዲጂታል አሰራሮችን በማስፋፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በከተሞች የዲጂታል አሰራሮችን በማስፋፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታኅሳስ 28/2015 በከተሞች የዲጂታል አሰራሮችን በማስፋፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ተናገሩ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር "ኢትዮጵያ 2050" የተሰኘው ተነሳሽነትን መነሻ ያደረገ ውይይት አካሄዷል።
ተነሳሽነቱ 2050 የሚኖረውን የህዝብ ቁጥር የሚያስተናግድ ዝግጅት ላይ ያተኮረ ሲሆን ፖሊሲ አውጪዎች፣ ስራ ፈጣሪዎች፣ ምሁራን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በአንድ በማሰባሰብ ወደ ፊት ሊያራምዱ የሚችሉ ሃሳቦችን ማፍለቅ የምክክሩ አጀንዳ ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በከተሞች የዲጂታል አሰራሮችን በማስፋፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ነው ብለዋል።
የኤሌክትሮኒክ ግብይት አዋጅ፣ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ፣ የጀማሪ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች (startup) አዋጅ፣ የግል ዴታ ጥበቃ አዋጅ፣ የዲጂታል መታወቂያ እና ሌሎችንም ምቹ ሁኔታዎችን መንግስት እየፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል።
እየጨመረ የሚሄደውን የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር የሚያስተናግድ የዲጂታል አሰራሮችን መዘርጋትና ለዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ውይይቱ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በአንድ መድረክ በማገናኘት የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እና አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የሚያስችል መሆኑን ይጠቁማል።