ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሰሜን ግንባር ለተመለሱ የፖሊስ አባላት የጀግና አቀባበል አደረገላቸው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 28/2015 የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሰሜን ግንባር ለተመለሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የፖሊስ አባላት የጀግና አቀባበል አደረገላቸው።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ለፖሊስ አባላቱ በተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት አቀባበል አድርገውላቸዋል።

“የኢትዮጵያ ፖሊስ ያለ ልዩነት እንደ ወታደርም የትኛውንም መስዋዕትነት ከፍሎ ሀገሩን ከማንኛውም የፀጥታ ችግር የሚታደግ መሆኑን አስመስክራችኋል” ብለዋል ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ፡፡

“ከሕዝብና መንግሥት የተጣለባችሁን አደራና ኃላፊነት በብቃት ስለተወጣችሁ በተቋሙና በራሴ ስም ላቅ ያለ ምስጋና ላቀርብላችሁ እወዳለሁ” ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስተባባሪነት በአንድ የፖሊስ አርማ በተሰማራበት ግዳጅ ሁሉ በትብብር መንፈስ፣ በአንድነት፣ በቁርጠኝነትና በታማኝነት አብሮ መስራት በመቻሉ በሀገር ደረጃ የፀጥታውን ስራ ውጤታማ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡

ግዳጅ የተወጡ ፖሊሶች አገርን በማስቀደም ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል በእኩልነት ማገልገል አለባቸው ነው ያሉት የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዝዳንት።

አገርን በማስቀደም ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል በእኩልነት ማገልገል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ኮሚሽነር ጀነራል ፖሊሶቹ በግዳጅ ላይ የቀሰሙትን ልምድና ተሞክሮ በአግባቡ በመጠቀም እና የዳበረ ፖሊሳዊ ስነ ምግባርን በማከል በክልላለቸው የተሻለ የፀጥታ ስራ እንዲያከናውኑም ጥሪ አቅርበዋል።

የተሰጣቸውን ግዳጅ በጀግንነት ለፈፀሙት የፖሊስ አባላት በእያንዳንዱ ሥም የተዘጋጀ የዕውቅና ሰርተፊኬት እንደሚሰጣቸውም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም