በድሬዳዋ ከተማ የገና በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ ከተማ የገና በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ
ድሬዳዋ (ኢዜአ) ታህሳስ 28/2015 በድሬዳዋ ከተማ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ማደረጉን የከተማው ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
መምሪያ የሕዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ባንታለም ግርማ በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ነገ የሚከበረው የገና በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ከዋዜማው ጀምሮ የቅንጅት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በተለይ ግብይት በሚካሄድባቸው የቀፊራ ፣የታይዋን እና የአሸዋ ገበያ ስፍራዎች ላይ የስርቆትና የፀጥታ ችግር እንዳይፈጠር ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ፖሊስ በበዓሉ ዋዜማና በዕለቱ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል አካባቢዎችን በተቀናጀ የሰው ኃይል ስምሪት የትራፊክ ፍሰቱ ሰላማዊ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሕብረተሰቡ በዓሉን ሲያከበር ከኤሌትሪክ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ቁሶች ሲገለገል ከእሳት አደጋ ራሱን በመጠበቅ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።
ህብረተሰቡ በበዓላቱ ወቅት ከመደበኛ እንቅስቃሴዎች ያፈነገጡና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲመለከት በስልክ ቁጥር 0251111600 ወይም በ0251115211 ወይም በ620 ላይ ደውሎ በመጠቆም ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ የድርሻውን እንዲወጣ ምክትል ኢንስፔክተር ባንታለም ጠቁመዋል።