የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እና የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማህበር በጋራ ለመስራት ተስማሙ

ታህሳስ 28/2015 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እና የኢትዮ-ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ ።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ጌቱ ግዛው እና ኢትዮ-ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ ባቡር ማህበር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብዲ ዘነበ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በባር ዘርፍ ልማት፣ ሀብት አስተዳደር፣ በእውቀት ሽግግር እንዲሁም በንግድ ትብብር ተቀናጅተው በመስራት ሀገራዊ የባቡር መስመሩን ውጤታማ ለማድረግ ያግዛል ተብሏል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብዲ ዘነበ ስምምነቱ የባቡር ዘርፉን እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በጋራ በመፍታት ዘርፍን በማነቃቃትና በማሳደግ አገርን በጋራ ማገልገል የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ምክትል ሰራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ጌቱ ግዛው በበኩላቸው ዘርፍን ሊለውጡ የሚችሉ ስራዎችን ለማከናወን እንደሚያግዝ ገልጸው በቀጣይ በሌሎች ዘርፎችም በትብብ እንደሚሰሩ ነው የጨመሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም