ሕዝበ ክርስቲያኑ የገና በዓልን ሲያከብር የተቸገሩትን በመንከባከብና በመደገፍ ሊያሳልፍ ይገባል-የኃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
ሕዝበ ክርስቲያኑ የገና በዓልን ሲያከብር የተቸገሩትን በመንከባከብና በመደገፍ ሊያሳልፍ ይገባል-የኃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 28/2015 ሕዝበ ክርስቲያኑ የገና በዓልን ሲያከብር የተቸገሩትን በመንከባከብና በመደገፍ እንዲሁም እርስ በእርስ በሰላምና በፍቅር ማሳለፍ እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች አሳሰቡ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያንና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ-ክርስቲያናት ካውንስል በነገው ዕለት የሚከበረውን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ባስተላለፉት መልዕክት ኅዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን በመተሳሰብና በመደጋገፍ ሊያከብረው ይገባል ብለዋል።
በዓሉ የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ የሚበስርበት እንዲሁም በእግዚአብሔርና በሰው ልጅ መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ የፈረሰበት መሆኑን በመገንዘብ በዓሉን በፍቅር ማሳለፍ ይገባል ነው ያሉት።
በዓሉ ትህትና የታየበት እንደመሆኑ መጠን ኅዝበ ክርስቲያኑ በተለያየ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ወገኖችን በማሰብና በማካፈል በዓሉን በአንድነት እንዲያከብር አሳስበዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ሠላም አምጥቷል ያሉት አቡነ ማትያስ በዓሉ የሰላምና የፍቅር እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው፤ የኢየሱስ ክርስቶስ በዓል የደስታ ምንጭ ነው፤ ህይወትን የሚወድ ሁሉ ልደትን ይወዳል ብለዋል።
በገና በዓል የህይወት ራስ የሆነው ክርስቶስ ተወልዷል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን በዓሉ የመተሳሰብና የሰላምና የፍቅር በዓል እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀኃፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ በበኩላቸው በዓሉ የዓለም ሰላም የሆነው ክርስቶስ የተወለደበት በመሆኑ በዓሉ የሰላምና የመተሳሰብ እንዲሁም የፍቅር እንዲሆን ምኞታቸውን ጠቁመዋል።