በጋምቤላ ክልል የገና በዓል በሠላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የገና በዓል በሠላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ
ጋምቤላ (ኢዜአ) ታህሳስ 28 ቀን 2015 በጋምቤላ ክልል ገናን ጨምሮ በቀጣይ የሚከበሩ በዓላት ህብረተሰቡ ያለምንም የጸጥታ ስጋት በሠላም እንዲያከብር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ ሩት ኩን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ከፌዴራል የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የጋራ ጥምር የጸጥታ ግብረ-ኃይል በማቋቋም ከክልል እስከ ወረዳ ስምሪት አድርጓል።
ይህም ነገ የሚውለው ገናን ጨምሮ በቀጣይ የሚከበሩ የጥምቀት በዓላትን ህዝቡ ያለምንም የፀጥታ ስጋት በሠላም እንዲያከብር ለማስቻል መሆኑን አስታውቀዋል።
እንዲሁም በግብይት ወቅትም የገንዘብና የሞባይል ንጥቂያዎች እንዳይከሰቱም በየገበያ ስፍራዎች የጸጥታ አካላት ተሰማርተው አስፈላጊውን ጥበቃ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በበዓል ወቅት አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲገጥሙት በአቅራቢያው ለሚገኙ የጸጥታ አካላት በመጠቆም እንዲተባበርም ጥሪ አቅርበዋል።