ቀጥታ፡

152ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ታሪካዊው ኤፍኤ ካፕ የዘንድሮ ዓመት ውድድር ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 28/2015 የዓለማችን አንጋፋው ብሔራዊ እግር ኳስ ውድድር የሆነው ኤፍኤ ካፕ ማንቸስተር ዩናይትድ ከኤቨርተን ዛሬ በሚያደርጉት ጨዋታ የዘንድሮ ዓመት መርሐግብር ይጀመራል።

ሁለቱ ክለቦች ከምሽቱ 5 ሰአት በኦልድ ትራፎርድ የሶስተኛ ዙር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ማንችስተር ዩናይትድ የኤፍኤ ካፕ ውድድርን 12 እንዲሁም ኤቨርተን 5 ጊዜ አንስተዋል።

ሁለቱ ክለቦች በኤፍኤ ካፕ ሲገናኙ የዛሬውን ጨምሮ ለ13ኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 12 ጨዋታዎች በተመሳሳይ ስድስት ጊዜ በመሸናነፍ አንዱ አንደኛውን ጥሎ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።

ማንችስተር ዩናይትድ እና ኤቨርተን በኤፍኤ ካፕ ሶስተኛ ዙር ሲገናኙ የዛሬው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የ38 ዓመቱ የዶንካስተር ተወላጅ ዳረን ኢንግላንድ የሁለቱን ክለቦች ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኤፍኤ ካፕ ሶስተኛ ዙር ጨዋታዎች ነገም ቀጥሎ ሲውል የአምናው የውድድሩ አሸናፊ ሊቨርፑል ከዎልቨርሀምፕተን ዎንድረርስ፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከፖርትስማውዝ እና ብሬንትፎርድ ከዌስትሃም ዩናይትድ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ተጠባቂ ናቸው።

ኤፍኤ ካፕ እ.አ.አ 1871 የተጀመረ አንጋፋ የእግር ኳስ ውድድር ነው።

የስፔን ላ ሊጋ 16ኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል።

ኤልቼ ከሴልታቪጎ ከምሽቱ 2 ሰአት ከ30 እንዲሁም ቫሌንሺያ ከካዲዝ ከምሽቱ 5 ሰአት ይጫወታሉ።

ነገ ቪያሪያል ከሪያል ማድሪድ ከምሽቱ 12 ሰአት ከ15 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የፊታችን እሁድ በሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም ከምሽቱ 5 ሰአት አትሌቲኮ ማድሪድ ከባርሴሎና የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

የ2022/23 የፈረንሳይ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ (ኩፕ ደ ፍራንስ) ውድድር ዛሬ በሶስተኛ ዙር ጨዋታዎች ይጀመራል።

ቻቴሩክስ ከፓሪሰን ጀርሜን ከምሽቱ 5 ሰአት ይጫወታሉ።

ስትራስቡርግ ከአንጀርስ፣ ግሬኖብል ከኒሜስ ኦሊምፒክ እና ፓዩ ከሞንፔሊዬ ዛሬ ከሚደረጉ የፈረንሳይ ጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች መካከል ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም