ተፎካካሪ ፓርቲዎች ኢህአዴግ ለውጡን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ጠንካራ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ተስፋ አድርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
ተፎካካሪ ፓርቲዎች ኢህአዴግ ለውጡን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ጠንካራ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ተስፋ አድርገዋል
አዲስ አበባ መስከረም 22/2011 በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ለውጡን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ከኢህአዴግ ጉባኤ እንደሚጠብቁ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ። በሃዋሳ ከተማ 'ነገ ይጀመራል' ተብሎ የሚጠበቀው የኢህአዴግ ጉባኤ በአባል ድርጅቶች መካከል ያለውን የውስጥ ልዩነት በመፍታት የለውጥ ሂደቱን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሚሆን እምነታቸው መሆኑን ፓርቲዎቹ አመልክተዋል። የመኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ኢዴህ፣ ኢዴአንና የኢሶዴፓ/መድረክ ከፍተኛ አመራር አባላት ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ኢህአዴግ ከሚያካሄደው ጉባኤ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግሮችን የሚፈቱ ውሳኔዎችን ይጠብቃሉ። የአገሪቷን መንግስት የሚመራው ኢህአዴግ የብሔር ግጭቶችንና የዜጎች መፈናቀልን ለማስቆም የሚያስችሉ ስልቶችን በመቀየስ እርምጃ ለመውሰድ የሚያበቁ ውሳኔዎችን ማሳለፍ እንዳለበት ነው የጠቆሙት። ከዚሁ ጋርም የህግ የበላይነትን በማክበር የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ለማክበር የሚያስችሉ ውሳኔዎች ከጉባኤው እንደሚጠብቁ ፓርቲዎቹ ገልፀዋል። የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ እንደገለፁት፤ ገዢው ፓርቲ በጉባኤው የሚያሳልፈው ውሳኔ አገሪቷ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያለፈችበትን የግጭቶችና የህግ ማስከበር እጥረት በዘላቂነት የሚፈታ መሆን አለበት። አቶ ዋሲሁን አክለውም ጉባኤው አገሪቷን ካለችበት ችግር አውጥቶ አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሚወስድ እንጠብቃለን ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኢዴህ) ምክትል ሊቀመንበር ገብሩ በርሄ በበኩላቸው፤ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች በአገሪቷ የሚነሱ ግጭቶችን ሲያባብሱ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህን ግጭቶች በዘላቂነት ለመፍታትና የተፈጠረውን ተስፋ ሰጪ ለውጥ ለማስቀጠል በጉባኤው አራቱም "የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ልዩነታቸውን እንዲፈቱ እንጠብቃለን" ብለዋል። በመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የሴቶች ጉዳይ ሃላፊ ወይዘሮ ሙሉ መኮነን፤ ከጉባኤው የግጭቶች መንስኤ እስከ መሆን የደረሱ "የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሔ የሚሰጥ ውሳኔ እንዲወሰን እጠብቃለሁ" ነው ያሉት። በተለይ የዜጎች ተዘዋውሮ የመስራትና ማህበረሰቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም የሚገባበት የተረጋጋ አስተማማኝ ሰላም ለመፍጠር የሚያስችል ውሳኔ ጊዜው የሚጠይቀው መሆኑን ተናግረዋል። የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን) አቶ ጉዕሽ ገብረስላሴ ደግሞ በጉባኤው በአገሪቷ የሚስተዋሉ ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችና የሰው ሕይወት መጥፋት ችግሮች ሊገታ የሚችል ውሳኔ መተላለፍ አለበት በማለት አሳስበዋል። አገሪቷን አደጋ ላይ እየጣለ ያለውን ይህን ግጭት ለማስቆም ገዢው ፓርቲ ጠንካራ ውሳኔ ማስተላለፍ ካልቻለ ሁኔታዎች ጥሩ አይሆኑም ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበርና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የሥራ አስፈፃሚ አባል ጥላሁን እንዳሻው በበኩላቸው፤ ከጉባኤው ችግር ያለባቸው የአገሪቷ የምርጫ ህጎችና አሰራሮች የሚስተካከሉበት ውሳኔ ይጠብቃሉ። የምርጫ ህጎችና አሰራሮች ማስተካከልና የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት በ2012 ዓ.ም እንዲካሄድ የሚጠበቀው ምርጫ "ተአማኒና ከውዝግቦች የፀዳ እንዲሆን ይረዳል" ያሉት አቶ እንዳሻው፤ በዚህ ረገድ "ከጉባኤው ጠንካራ ውሳኔ እንጠብቃለን" ብለዋል። የ11ኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ "አገራዊ አንድነት፤ ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሀሳብ ከነገ መስከረም 23 ቀን ጀምሮ ለሶስት ቀናት በደቡብ ክልል ሀዋሳ ከተማ ይካሄዳል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።