"ክሮፕኮኔክስ" የተሰኘው ኩባንያ የኢትዮጵያ ቡናን በኢ-ኮሜርስ አማካኝነት ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ የሚያስችለውን ፈቃድ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
"ክሮፕኮኔክስ" የተሰኘው ኩባንያ የኢትዮጵያ ቡናን በኢ-ኮሜርስ አማካኝነት ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ የሚያስችለውን ፈቃድ አገኘ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 27/2015 "ክሮፕኮኔክስ" የተሰኘው የአሜሪካ ኩባንያ የኢትዮጵያ ቡናን በኢ-ኮሜርስ አማካኝነት ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ የሚያስችለውን ፈቃድ አገኘ፡፡
በዚህም "ክሮፕኮኔክስ" የተሰኘው የአሜሪካ የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ሥርዓት አንቀሳቃሽ ኩባንያ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኢ-ኮሜርስ ንግድ መደብ ፍቃድ ያገኘ ድርጅት ሆኗል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና "ክሮፕኮኔክስ" በኤሌክትሮኒክስ ንግድ መሰረት የኢትዮጵያ ቡና ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ እየተደረገ ያለውን ዝግጅት በሚመለከት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሁሪያ ዓሊ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በርካታ የንግድ ድርጅቶች ወደ ኤሌክትሮኒክስ ንግድ እየገቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
መሠረቱን በአሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ከተማ ያደረገው የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ሥርዓት አንቀሳቃሽ ኩባንያ "ክሮፕኮኔክስ" በኢ-ኮሜርስ አማካኝነት የኢትዮጵያ ቡናን እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ሥርዓቱ የቡና አምራችና ላኪዎችን ቀጥታ ከተጠቃሚው ጋር እንደሚያገናኝ ወይዘሮ ሁሪያ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ተደራሽ ያልሆነባቸውን አካባቢዎች አዲስ ገበያ ለማግኘትና በዓለም ዙሪያ ለማስተዋወቅ ሥርዓቱ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርም ነው የተናገሩት፡፡
ይህም ለቡና አምራቾችና ላኪዎች ትልቅ ዕድል መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ክሮፕኮኔክስ የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ሥርዓት በንግድ ዘርፍ ለሚሰማሩ ሌሎች ድርጅቶችም ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
ኩባንያው ግብር ከፋይና የኤሌክትሮኒክስ ኮሙኒኬሽን ድንጋጌዎችን ለማክበር የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቶለት የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የፈጣን መልዕክት አገልግሎት ሰጪዎች በኤሌክትሮኒክስ ንግድ ውስጥ ያላቸው ሚና ዕውቅና እንዲሰጣቸው በአዋጅ መደንገጉን ወይዘሮ ሁሪያ አስታውሰዋል።
ሥርዓቱ የቡና አምራቾችን በማደራጀት፣ በማስተዋወቅና ቡናን ለሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ገዥዎች ለማስተዋወቅና ለመሸጥ እንደሚያግዝ የተናገሩት ደግሞ የኩባንያው ባለቤት ብሪያና ዲኬይ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሂደት ውስጥ የተለያዩ ተዋናዮች የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እንደሚያነሳሳም ጠቁመዋል።
የቡና ንግድ በፍጥነት እያደገ በመሆኑ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሥርዓቱ የተቀናጀ ሽያጭና አቅርቦት እንዲኖር እንደሚያግዝም ጨምረው ገልጸዋል፡፡