የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ዘላቂ እንዲሆን የህበረተሰቡ ተሳትፎ ተጠየቀ

ሐዋሳ (ኢዜአ) ታህሳስ 27 ቀን 2015 የሐዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ የአካባቢው ማህበረሰብ ተሳትፎ ተጠየቀ።

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ  የተረጋጋ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ለአምራች ኢንዱስትሪው ምቹ ማድረግ ላይ ያተኮረ ውይይት ከአካባቢው ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ዛሬ በፓርኩ ቅጥር ግቢ ተደርጓል።

የፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ ማቲዎስ አሸናፊ በወቅቱ እደገለፁት፤ ፓርኩ ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር በማረጋገጥ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል።

በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እያበረከተ የለውን አስተዋጽኦ ቀጣይነት ለማረጋገጥ የአካባቢውን ማህበረሰብ ያሳተፈ ስራ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በፓርኩ ውስጥ ባሉ 52 ሼዶች  በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ 23 አምራች ኩባንያዎች እንዳሉ ገልጸው፤ በእንቅስቃሴያቸውም ከ28ሺ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ጠቅሰዋል።

በፓርኩ ያሉ አምራቾችና ሰራተኞቹ ውጤታማ ስራ እንዲያከናውኑ ፓርኩን የተረጋጋና ደህንነቱ የተጠበቀ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የፓርኩን ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ በዙሪያው ያለው የአካባቢው ማህበረሰብ ድርሻ ከፍተኛ ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ ህብረተሰቡ በእኔነት ስሜት ፓርኩን እንዲጠብቀው ጠይቀዋል።

በፓርኩ የስራ እድል የተፈጠረላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችም በፓርኩ የሚያገኙት የስራ ክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋቸው መገንዘብ አለባቸው ብለዋል።

በቀጣይ የራሳቸውን ስራ መጀመር የሚያስችላቸውን አቅም አጎልብተው ኢንዱስትሪውን የሚቀላቀሉበት እድል መፍጠር እንደሚችሉ ጠቅሰው፤ 30 የሚደርሱ የፓርኩ ሰራተኞች የራሳቸውን ስራ መፍጠራቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡

የውይይቱ ዓላማ የፓርኩን ደህንነት በማስጠበቅ ምርታማነቱን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የማህበረሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ምክትል ስራ አስኪያጁ አቶ በልአንተ ጠብቀው ናቸው።

በፓርኩ አካባቢ የሚያጋጥሙ ጥቃቅን የስርቆት ወንጀሎችን በመከላከል ህገ ወጦችን በህግ ማስጠየቅና በዙሪያው የሚኖሩ የፓርኩ ሰራተኞችን ደህንነት መጠበቅ ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም