ቀጥታ፡

የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል ከ3 መቶ ለሚበልጡ ህጻናት የልብ ቀዶ ህክምና መስጠቱን ገለጸ

አዲስ አበባ ታህሳስ 27/2015 (ኢዜአ) ፦በጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል ከ3 መቶ በላይ ለሚሆኑ ህጻናት የልብ ቀዶ ህክምና መስጠቱን ገለጸ።

የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል የ2022 የሥራ ዘመን በልብ ማዕከል ውስጥ የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም በልብ ማዕከሉ ለ8 ሺህ,674 ሕሙማን የልብ ሕክምና ክትትል እንዲሁም ለ328 ሕሙማን የልብ ቀዶ ሕክምና እና በደም ስር በኩል የሚከናወን የልብ ሕክምና አገልግሎት በነፃ ለመስጠት መቻሉ ተገልጿል፡፡

የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሚክሎል መንግስቱ እንዳሉት ይህ ቁጥር ከማዕከሉ የመስራት አቅም እና ወረፋ ከሚጠብቁ ሕሙማን ቁጥር አንፃር እጅግ አነስተኛ አገልግሎት ቢሆንም ከሕብረተሰቡ እና ከተለያዩ ተቋማት በተገኘው ድጋፍ አገልግሎቱን ማስቀጠል ተችሏል፡፡

የድርጅቱ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር አርቲስት መሠረት መብራቴ፣ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሳላሃዲን ከሊፋና የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ሕክምና ካገኙ ሕፃናትና ወላጆች ጋር በጋራ በመሆን ድጋፍ ላደረጉ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት ለሚገኙ ግለሰቦች እንዲሁም የግልና የመንግስት ተቋማት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በልብ ማዕከል ውስጥ በአሁኑ ሰዓት ከ7,400 በላይ ሕሙማን ወረፋ በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ ከማዕከሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ማዕከሉን በ6710 አጭር የፅሁፍ መልዕክት ላይ “OK” ብሎ በመላክ ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም