በፍርድ ቤቶች የሚሰሩ ሴት ሠራተኞች ተሳትፎን ለማሳደግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል-የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት - ኢዜአ አማርኛ
በፍርድ ቤቶች የሚሰሩ ሴት ሠራተኞች ተሳትፎን ለማሳደግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል-የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 27/2015 በፍርድ ቤቶች የሚሰሩ ሴት ሠራተኞች ተሳትፎን ለማሳደግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ ገለጹ፡፡
ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በፍርድ ቤቶች የሥርዓተ-ፆታና ፍትሕ ተደራሽነት ላይ የተደረጉ ጥናቶችን አስመልክቶ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ፍርድ ቤቱ ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ የለውጥ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተዋል፡፡
ከእነዚህም መካከል በፍርድ ቤቶች ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ማጎልበት አንደኛው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም በፍርድ ቤቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ የሚገኙ ሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እና ሴት ሠራተኞችን ከፆታዊ ትንኮሳ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
በአገሪቱ በሦስቱም ደረጃ በሚገኙ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሴት ዳኞችን የመሾምና ወደ አመራር ደረጃ እንዲበቁ ማድረግ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በተለይም በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ፆታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት የሁሉንም ተቋማት ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ፆታን መሰረት አድርገው የሚፈጸሙ ወንጀሎች ክርክርን ውጤታማ ለማድረግ የመርሃ-ችሎት (ቤንች ቡክ) መጽሐፍ፤ የፆታ ትንኮሳ መከላከያ ፖሊሲ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡
በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሰብሳቢ ዳኛ እትመት አሰፋ በበኩላቸው፤ የተደረገው የዳሰሳ ጥናት በፍርድ ቤቶች የሚሰሩ ሴቶች ሊደርስባቸው ከሚችል ፆታዊ ጥቃት ለመጠበቅ ያለመ ነው።
እንዲሁም ፍትሕ ለማግኘት ለሚመጡ ሴቶች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል፡፡