ወደ አገራቸው ከተመለሱ የፖለቲካ ቡድኖች ጋር ለመስራት ዝግጁ ነኝ - ኢዴፓ - ኢዜአ አማርኛ
ወደ አገራቸው ከተመለሱ የፖለቲካ ቡድኖች ጋር ለመስራት ዝግጁ ነኝ - ኢዴፓ
አዲስ አበባ መስከረም 22/2011 "ወደ አገራቸው ከተመለሱ የፖለቲካ ቡድኖች ጋር ለመስራት ዝግጁ ነኝ" ሲል የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ገለፀ። የኢትዮጵያ ህዝብ ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለምና አደረጃጀት ያላቸው ፓርቲዎች መሰባሰብ ይችሉ ዘንድ በጎ ግፊት እንዲያደርግም "ልዩነትን ማክበር፣ መቻቻልና ምክንያታዊነት የስልጡን ፖለቲካ መርህ ነው" ሲል ባወጣው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል። ባለፉት ጥቂት ወራት በውጭ አገራት የነበሩ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ወደአገር ቤት መመለሳቸው ይታወቃል። የፖለቲካ ድርጅቶቹ ወደአገር ቤት መመለስ ለብዙሃን ፓርቲ ስርዓት መጠናከር፣ ለምክንያታዊና የመቻቻል ፖለቲካ መጎልበት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል ሲል ነው ኢዴፓ ያመለከተው። ኢዴፓ ከእነዚህ ፓርቲዎች ጋር ለአገር፣ ለህዝብና ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ተባብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑንም አስታውቋል። "ኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ዓመታት ሰላማዊ ትግል በማድረግ ላይ ያለን ፓርቲዎች የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ ለውጥ በመጠቀም ድክመቶቻችንን መገምገምና ድርጅታዊ መዋቅራችንን በመፈተሽ ራሳችንን ማጠናከር አለብን" ሲል ገልጿል። በኢትዮጵያ ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ እንዲፈጠር የሚጠበቅበትን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንንም አክሏል። ፓርቲው "አሁን ያለውን ድርጅታዊ አቅም በገዥው ፓርቲ ላይ ትርጉም ያለው ተፅዕኖ ለማሳደር፤ የህዝብን ትግል በአግባቡ ለመምራት የምንችልበት ባለመሆኑ መተባበርና መጠናከር ይኖርብናል" ብሏል። ህዝቡ ያለድርጅታዊ አመራርና ያለጠንካራ ፓርቲ የሚካሄድ የፖለቲካ ትግል የትም ሊያደርስ እንደማይችል ተረድቶ ተመሳሳይ ርዕዮተዓለምና አደረጃጀት ያላቸው ፓርቲዎች እንዲሰባሰቡ በጎ ግፊት እንዲያደርግም ጥሪ አቅርቧል። መንግስትም ያለጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን እውን ማድረግና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት እንደማይቻል በመረዳት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች መጠናከር ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንዳለበት አሳስቧል። ምሁራን በሚያምኑባቸው ፓርቲዎች ውስጥ በስልጠና፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በአባልነትና በአመራርነት በመሳተፍ ፓርቲዎችን እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርቧል። የሲቪክ ማህበራት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የዲፕሎማቲክ ተቋማት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውን ለማገዝ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም እንዲሁ። የተጀመረው ለውጥ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ወጣቶች ለውጡን ወደፊት በሚያስኬዱ ተግባራት ላይ እንዲያተኩሩም ጠይቋል ኢዴፓ። በየትኛውም ወገን የተፈፀሙ ተግባራትን በማንሳት የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ይኖራል ብሎ እንዳማያምን አስታውቆ ይህን ተግባር በመፈፀም የተጀመረውን ለውጥ ወደኋላ ለመመለስ የሚጥሩ አካላት ከድርጊታቸው ይታቀቡ ብሏል። የስርዓት ለውጥ ለማምጣት የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ድርጅቶች ከመንግስት ጋር በመደራደር ወደአገር ቤት ቢገቡም የተስማሙባቸው ነጥቦች ለህዝቡ መገለፅ እንዳለበትና መንግስት በዚህ ዙሪያ አስቸኳይ መግለጫ ሊሰጥ እንደሚገባም ኢዴፓ በመግለጫው ጠይቋል።