ቀጥታ፡

ኢትዮ-ቴሌኮም እና ጌትፋክት ኢትዮጵያ የተሰኘ ድርጅት በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ (ኢዜአ)ታህሳስ 27/2015 ኢትዮ-ቴሌኮም እና ጌትፋክት ኢትዮጵያ የተሰኘ ድርጅት የዲጂታል መማሪያ ማዕከላትን በመጠቀም የተማሪዎችን ክህሎት የሚያሳድጉ ሥልጠናዎችን መስጠት የሚያስችል የጋራ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ እና የጌትፋክት ኢትዮጵያ መሥራችና የናሳ ተመራማሪ ዶክተር ብርሃኑ ቡልቻ ናቸው የተፈራረሙት።

በስምምነት ፊርማው ወቅት አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሃመድ እንድሪስና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም እና ጌትፋክት ኢትዮጵያ ያደረጉት ስምምነት የተለያዩ ሥልጠናዎችን ለከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በትብብር መስጠት የሚያስችል፣ "ብሩህ ትውልድ" የተሰኘ የትምህርት ፕሮግራም በጋራ ለማስኬድ መሆኑ በፊርማ ስነ-ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል።

ስምምነቱ በሁለቱ ተቋማት የጋራ ፍላጎት ጠንካራ አጋርነት በመፍጠር በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ምሁራንን በማሳተፍ መሥራት ያስችላልም ተብሏል።

የእውቀት ሽግግርን በማምጣት ማዕከላቱ የተቋቋሙበትን ዓላማ ማሳካት እንዲችሉ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ተገልጿል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚሁ ወቅት፤ ቴሌኮሙ ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የተያዘው መንገድ እንዲሳካ ትውልድን መገንባት ላይ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል ብለዋል።

በዚህም ኢትዮ-ቴሌኮም ከዚህ ቀደም ባቋቋማቸው የዲጂታል መማሪያ ማዕከላት አማካኝነት ሥልጠናውን በተገቢው መልኩ ለመስጠት የሚያስፈልጉ ሙያዊና የቴክኖሎጂ እገዛ የሚያደርግ እንደሆነ ገልጸዋል።

እንደ አስፈላጊነቱም ሥልጠናዎች በበይነ-መረብና በገጽ-ለገጽ እንዲሰጡ ድጋፍ የሚያደርግ እንደሆነም ጨምረዋል።

የጌትፋክት ኢትዮጵያ መሥራችና የናሳ ተመራማሪ ዶክተር ብርሃኑ ቡልቻ በበኩላቸው፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን በእውቀት ሽግግር ለማገዝ ታስቦ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

በዚህም ጌትፋክት ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን በእውቀት ለማሻገር ይህ መልካም ዕድል መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በዚህም የሀገር ተረካቢ ወጣቶችን በእውቀት ለማስታጠቅ የሚረዳ እንደሆነም ተናግረዋል።

ስምምነቱ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር አጫጭር እና ለውጥ የሚያመጡ የተግባቦት፣ የቋንቋ፣ የጥልቅ አስተሳሰብ፣ የአመራርና የኮምፒዩተር ፕሮግራሚንግ ሥልጠናዎችን መስጠት የሚያስችል እንደሆነም አስረድተዋል።

በቀጣይም ለዲጂታል መማሪያ ማዕከላቱ የሚያስፈልጉ የትምህርት ግብአቶችን የማሟላት፣ የኃይል አቅርቦት አማራጮችን የማቅረብና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በማሟላት በኩል በትብብር መሥራት የሚያስችል ይሆናል ተብሏል።

አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የነገው ትውልድ ለኢትዮጵያ እንደሚጠቅምና የዓለም የዲጂታል ምህዋር ውስጥ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ይህ በጎ ጅማሮ ነው ብለዋል።

ጌትፋክት ኢትዮጵያ ነዋሪነታቸውን በውጭ ሀገራት ያደረጉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ያቋቋሙት  ሲሆን፤ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅና በጎ አመለካከቶች እንዲዳብሩ ለማድረግ የሚሰራ ድርጅት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም