ገና እና ላሊበላ

1077

(ብርሃኑ  አለማየሁ)

በኢትዮጵያ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ወይም ገና አንዱ ነው።

በዓሉ በሃይማኖት ተቋማቱ ሃይማኖታዊ ስርዓትና ትውፊት መሰረት ይከበራል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ በሚከናወኑ የዝማሬና የመንፈሳዊ የጸሎት መርሐ ግብሮች አማካኝነት በዓሉ በልዩ ሁኔታ ይከበራል።

የገና በዓል በቤተክርስትያኗ ስርዓትና ትውፊት በተለየ ሁኔታ ከሚከበርባቸው ስፍራዎች ቀዳሚው በሰሜን ወሎ ዞን አገረ ስብከት ስር የሚገኘው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ነው።

የላሊበላ አካባቢ የመሬት አቀማመጡ ለግብርና ባይጋብዝም፤ ፍሬያማነቱ  በታላላቆች የጥበብ ንቃት የሚለካና ምርታማነቱም ባኖሩት የኪነ-ህንጻ ርቀት የሚመነዘር እንዲሆን አድርጎታል። ጥልቅ የኪነ ህንጻ ጥበብ ያረፈባቸው ዘመን ተሻጋሪዎቹ  የላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ፤ የቆየውን ሀይማኖታዊ ህይወትና ክንዋኔ ፈጣን በሆነው የዓለም ለውጥ ሳይበረዝ እንዲቀጥል ጠባቂ በመሆንም ወደር አይገኝላቸውም ፡፡

ቅዱስ ላሊበላ /ከ1180­-1207 ዓ.ም/ ከአባቱ ጃን ስዩም እና ከእናቱ ኪርወርና ይባላሉ። በተወለደም ጊዜ በንብ ስለ ተከበበ እናቱ ማር ይበላል ለማለት "ላል ይበላል" ብላለች። በአገውኛ “ላል” ማር ማለት ነው። ከዚህ የተነሳ ስሙ “ላልይበላ” ተባለ።

ቀደም ሲል ሮሀ በአሁኑ አጠራር ላሊበላ በመባል የሚታወቀው ቦታም ስያሜውን ያገኘው እንደ እ.ኤ.አ ከ1181-1221 ነግሶ ከነበረው የመጀመሪያው የዛግዌ ስርወ - መንግስት ንጉስ ላሊበላ መሆኑ ይነገራል፡፡  

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስርዓት መሰረት የቅድስና ማዕረግ ከተሰጣቸው ነገሥታት መካከል አጼ ላሊበላ አንዱ ሲሆን፤ የተወለደበት ዕለት ታህሳስ 29 መሆኑን ገድሉ ይገልጻል። በዚህም የኢየሱስ ክርስቶስ እና የቅዱስ ላልይበላ የልደት በዓል በላልይበላ በጥምረት ይከባራል።

የበዓሉ በጥምረት መከበርን አስመልከቶ ከታህሳስ 28 ከምሽት 2 ሰዓት ጀምሮ የሚካሄደው ሰርዓተ ማኅሌትና ዝማሬ  ከዓለት ወደታች በሰው እጅ የተፈለፈሉትን አብያተ ክርስትያናት በተመስጦና በአድናቆት ለሚመለከተው ጎብኚ ሌላ ማራኪ ትዕይንት ይሆንበታል።

በዓሉ ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ በሆነው ቤተ መድኃኔዓለም የሚከበር ሲሆን፤ የቤተ ክርስቲያን መረጃዎች በተባለው መጽሐፍ እንደተገለጸው  ይህ ቤተ መቅደስ ቅዱስ ላሊበላ በሮሐ ከዓለት ከፈለፈላቸው አብያተ ክርስቲያናት አንዱ ነው።

በዓሉም በዚህ ቤተ መቅደስ በአካባቢው ካሉ አብያተ ክርስቲያናት ከተውጣጡ ከ500 በላይ አገልጋዮች  ህብረ ዝማሬ ማህሌት (ምስጋና) የሚታሰብ ይሆናል። አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ መጽሐፋቸውና በዓሉን አስመልክቶ ከታተመው ሐመር መጽሔት እንደተመለከተው የገና በዓል አከባበር የሚጀምረው ከታህሳስ 23 (በዓለ ጊዮርጊስ) አንስቶ ሲሆን፤ እስከ ታህሳስ 29 ድረስ ይቀጥላል።

የማኅሌቱን ስነ ስርዓት ስንመለከት አንድ ጊዜ 12 ገደማ ጥንግ ድርብ የለበሱ በአንድ በኩል ደግሞ ጥቁር ካባ የለበሱ ማኅሌታውያን እያሸበሸቡ ስርዓተ ማኅሌቱን ያከናውኑታል። ማዕጠንት የያዙ 4 ካህናትና ከ8 ያላነሱ ዲያቆናት ወርቅ ካባ ለብሰው፣ የወርቅ አክሊል ደፍተው፣ የወርቅ መስቀል ይዘው መለከት እየነፉ ዙሪያውን በመዞር ማህሌቱን ያጅቡታል።

ይህ ታህሳስ 28 ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀመሮ የሚከናወነው የማኅሌት ሰርዓት ሌሊት 10 ሰዓት ላይ በሰርዓተ ቅዳሴ ይተካና ታህሳስ 29 ቀን ከ12 ሰዓት ጀምሮ ደግሞ ከ11ዱ የላልይበላ ቤተ መቅደስ የተውጣጡ ሊቃውንት የበዓሉን ያሬዳዊ ዜማ ለማጀብ ወደ ማሜ ጋራ /ቤዛ ኩሉ ዓለም ሥነ ሥርዓት የሚካሄድበት ቦታ/ ይወጣሉ።

ልክ አንድ ሰዓት ሲሆን፤ ከላይና ከታች የሚሰለፉ ካህናት ቦታቸውን ይይዙና እስከ 4 ሰዓት በሚፈጅ ክንውን እየተቀባበሉ ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ' የዓለም መድሃኒት ዛሩ ተወለደ የተባለውን ወረብ ያቀርባሉ። የበዓሉን አከባበር በላሊበላ ልዩ የሚያደርገው አንዱ ይህ “ቤዛ ኩሉ ዓለም" የሚባለው የቀለም ዓይነት ሲሆን፤ በወረቡ ትርጓሜ መሰረት ዝማሬው ለአገር፣ ለወገን፣ ለምድር ሰላም በረከት የሚጸለይበት ነው።

ከትርክቱም በላይ ዛሬም ድረስ ተአምራዊ ጥበባቸው ያልተፈታው የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ዓለምን ማስደመማቸው እንደቀጠለ ፤ ታላቅነታቸው እንደቀደመ፤ ቅድስናቸው እንደጸናና  የበርካታ ሰዎችን የመንፈስ ቀልብ እንደገዙ ከሚታሰበውም በላይ ልቀው የዘለቁ ናቸው። 

የገናን በዓል በላሊበላ ለመታደም እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናቱንና መንፈሳዊ የበዓል ሥርዐቱን ለመጎብኘት  የሃይማኖቱ ተከታዮችና በርካታ አገር ውስጥና የውጭ አገር ጎብኚዎች ወደ ላሊበላ ያቀናሉ።

ላሊበላ ከተማ አብዛኛውን የኢኮኖሚ ምንጯንና ማህበራዊ መስተጋብሯን መሰረት ያደረገቸው ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጎብኚዎችና እሱን ተከትሎ ባሉ የማህበራዊ ትስስር ጉዳዮች ነው ቢባል ማጋነን አየሆንም።

በርካታ ጎብኚዎችም የአብያተ ክርስቲያናቱን የኪነ ህንጻ  ልህቀት ከሀይማኖታዊ ክንዋኔው ጋር ለማጣጣም ገናንን ተከትሎ የሚመጣውን የጥምቀት በዓል ተመራጭ ያደርጋሉ፡፡

በዓላትን ተከትለው በሚቆሙት ገበያዎቹ ፤ ከመቶ ዓመታት በላይ እንዳስቆጠሩ በሚነገርላቸው ልዩ ባለአንድ ፎቅ መኖሪያ ቤቶች በአካባቢው ነዋሪዎች አጠራር “ህድሞ” በሚባሉት ሳይቀር መስህብነቱን ከፍ ያደረገ ነው፡፡

በዓሉን ለመታደምና ስለታቸውን ለመፈጸም የሚመጡ እንግዶች ላሊበላ የምትጠቀምበት መንገድም ሌላኛው አስደናቂ መስህብ ነው። የገና በዓል ከመከበሩ ሳምንታት በፊት አስቀድመው ወደ ላሊበላ የሚመጡ ሰዎችን እግር በማጠብ፣  ቤት ያፈራውን በማቅረብ ለዘመናት ያካበተ እሴት በአደባባይ ይገለጣል።

በስፍራው ከሚገኙ ሁቴሎች ጀምሮ ቅርጻ ቅርጽ ሻጮችና ሌሎች ዘርፎች በገና ወቅት ገበያ የገበያ አድማሳቸው የሚሰፋ ይሆናል። ነዋሪውም ቢሆን በወደደው የእጅ ጥበብ የተካነ ፤ ከአባቶቹ በወረሰው ጥንታዊ የብራና ላይ ጽሁፎቹና  ስዕሎቹ የደመቀና ከዘመናት በፊት ከጥበበኞቹ የወረሰውን ጥበብ በስጦታዎቹ ላይ የራሱን አሻራ ጨምሮ ይታያል፡፡

በላሊበላ በገና ሰሞን ከሚታዩ አስደናቂ ሁኔታዎች መካከል ተጠቃሽ የሚሆነው ደግሞ በዓሉን አስታኮ የሚከናወነው የሰርግ ስነ ስርዓት ነው። የላሊበላ ጎብኚና ተሳላሚ እድምተኛ የሚሆንበት ሰርግ።

በሰርግ ስነ ስርዓቱ ቤተ ዘመድ ተሰባስቦ ፍቅርን የሚለዋወጥበት፣ ስለ ማህበራዊ ጉዳዮች የሚመክርበት ብሉልኝ ጠጡልኝ የሚልበት የላሊበላን እንግዳ በፍቅር ማዕድ የሚያስቀድስበትም ነው። ይህም የገና በዓል በላሊበላ ሃይማኖታዊ፣ መንፈሳዊ፣ ትውፊታዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አገራዊ ፋይዳ እንዳለው የሚያመለክት ነው።

ዓለምን በአንድ የሚያናግሩት ቅርሶች መገኛ የሆነው ላሊበላ ለነዋሪውም፡ ለመላው ህዝብም ለጎብኚዎችም ተመችቶ እያስደመመ እንዲቀጥል ቅርሶቹን መጠበቅና የአካባቢውን መሰረተ ልማት ማሟላት ያሻል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም