ዘመናትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያዊያን በሰላም በፍቅርና በአብሮነት የመኖር እሴትን ማጠናከር ይገባል---አቶ ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
ዘመናትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያዊያን በሰላም በፍቅርና በአብሮነት የመኖር እሴትን ማጠናከር ይገባል---አቶ ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ ኢዜአ ታህሳስ 27/2015 ፦ዘመናትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ህዝቦች በሰላም በፍቅርና በአብሮነት የመኖር እሴትን ማጠናከር እንደሚገባ የሲዳማ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳደሩ ለክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ ደስታ የገና በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ ላይ ሁሉም ወደ ቀልቡ ተመልሶና ፍቅር ኖሮት መጠያየቁን፣ መከባበሩን አንድነቱና አብሮነቱን በማጎልበት በዓሉን ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዘመናትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ህዝቦች በሰላም በፍቅርና በአብሮነት የመኖር እሴትን ማጠናከር ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ነው ሲሉም ገልጸዋል።
እምነቱ በሚያዘው መንገድ "እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ" የሚለውን ትእዛዝ መተግባር ብንችል ጥላቻ፣ መገፋፋት፣ መፈናቀልና አንዱ አንዱን መበደል ሊነግስ ባልቻለ ነበርም ብለዋል።
በአዲስ መንፈስ እና አስተሳሰብ የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆንም ሁሉም በተሰማራበት መስክ ጠንክሮ እንዲሰራም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በዓሉን የተቸገሩ ወገኖችን በማብላትና በማጠጣት የተለመደ የመተዛዘን እና የመረዳዳት ባሕልን በተገበረ መልኩ መሆን እንዳለበት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዓሉ በሀዋሳና በሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም ርዕሰ መስተዳድሩ ጨምረው ገልጸዋል።