ቀጥታ፡

ማህበራትና ባለሀብቶች የመሰረተ ልማትና የባንክ ብድር አገልግሎት ችግር እንዲፈታላቸው ጠየቁ

ጋምቤላ (ኢዜአ) ታህሳስ 27/2015 በጋምቤላ ክልል በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ላይ የተሰማሩ ማህበራትና ባለሀብቶች የመሰረተ ልማትና የባንክ ብድር አገልግሎት ችግር እንዲፈታላቸው ጠየቁ።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ከክልሉ ንግድ ቢሮ ጋር በመቀናጀት የአነስተኛና የመከከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ለማጠናከር በጋምቤላ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ አካሄዷል።

በመድረኩ ከተሳተፉ ባለሃብቶች መካከል በማጃንግ ዞን በቡና ማቀናበር ዘርፍ ላይ የተሰማሩት አቶ በየነ ብርሃኑ በተሰማሩበት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ስራቸውን ለማጠናከርና ለማስፋፋት የኤሌክትሪክ፣ የመንገድና የብድር አገልግሎት ተግዳሮት ሆኖባቸዋል።

በአካባቢው የሚመረተውን የሰሊጥ፣ አኩሪ አተርና ሌሎች የቅባት እህሎችን ታሳቢ በማድረግ የዘይት ፋብሪካ ለማቋቋም እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በዲማ ወረዳ በእርሻና ሆቴል ኢንቨስትመት የተሰማሩ ባለሃብት አቶ ሰለሞን አክሎክ ናቸው።

ለማቋቋም ላሰቡት የዘይት ፋብሪካ የሚሆን የማሽን መግዣ ብድር ጥያቄ አቅርበው ምላሽ ማጣታቸውን ተናግረዋል።

ሌላው ተሳታፊ አቶ ድንገቱ ራጰሽ በግላቸውና በማህበር በመደራጀት በዳቦ ማምረትና በቡና እርሻ ልማት በመሰማራት እራሳቸውና አካባቢያቸውን ለመጥቀም ቢሞክሩም የባንክ የብድር አገልግሎት ችግር እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል።

"በክልሉ በአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ዘርፍ ማነቆ የሆነው የብድር አገልግሎት ችግር ሊፈታ ይገባል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን ተካልኝ የተነሱ ጥያቄዎችን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ "ባንኩ የፕሮጀክትና የሊዝ ፋይናንስ የብድር አገልግሎት መስፍርቱን አሟልቶ የሚመጣ ብድር ጠያቂን ለማስተናገድ ዝግጁ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ መርጋ በበኩላቸው እንደ ሀገር ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለብድር አገልግሎት የሚውል 200 ሚሊዮን ዶላር መኖሩን ተናግረዋል ።

በመረጃና በቴክኒክ ችግር ምክንያት መስፈርት አሟልተው ወደ ልማት ባንክ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የሚመጡት የክልሉ ኢንተርፕራይዞች ውስን መሆናቸውን ጠቁመው "በዘርፉ ሰፊ የግንዛቤ ስራዎች ማከናወን ይገባል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሴ በበኩላቸው በተለይም በጋምቤላ ያለውን ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት ወደ ልማት በመቀየር ሀብቱን ጥቅም ላይ ለማዋል ሁሉም አካል በቅንጅትና በትብብር መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በክልሉ በኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ጅምር ስራዎች ቢኖሩም የተፈለገውን ያህል አለመሆኑን ጠቁመው በክልሉ እስከአሁን 80 ኢንተርፕራይዞች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ በበኩላቸው "በባለሃብቶችና ማህበራት የቀረቡትን የተለያዩ የመሰረተ ልማት አውታሮች ችግር ደረጃ በደረጃ በመፍታት አምራች ኢንዱስትሪውን ለማስፋትና ለማጠናከር የክልሉ መንግስት በትኩረት ይሰራል" ብለዋል።

በጋምቤላ ከተማ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ለማጠናከር ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ሀላፊዎች፣ የፌዴራልና የሚመለከታቸው ተቋማት ተጠሪዎች፣ ባለሃብቶችና ማህበራት ተሳትፋዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም