በምሥራቅ ወለጋ ዞን እስካሁን ከተሰበሰበው ሰብል 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በምሥራቅ ወለጋ ዞን እስካሁን ከተሰበሰበው ሰብል 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኘ
ነቀምቴ (ኢዜአ) ታሕሣሥ 27/2015 በምሥራቅ ወለጋ ዞን እስካሁን ከተሰበሰበው ሰብል 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ የአዝርዕት ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ፋንታ አሰበ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ በ2014/2015 የመኸር ምርት ዘመን 400 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያየ ሰብል ለምቷል።
በዞኑ የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ ለመሰብሰብ በተደረገው ጥረት እስካሁን በ336 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የነበረ የደረሰ ሰብል ተሰብስቧል ብለዋል፡፡
ቡድን መሪው እንዳሉት እስካሁን ከተሰበሰበው የደረሰ ሰብል 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የተገኘ ሲሆን፤ የቀረውን የደረሰ ሰብል ምርት ለመሰብሰብ በቅንጅት እየተሰራ ነው።
በአካባቢው አሁን እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሰ ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶ አደሩ በቤተሰብ፣ በልማት ቡድን እና ተማሪዎችን በማሳተፍየደረሱ ሰብሎች እየሰበሰበ ነው ብለዋል፡፡
በዚሁ መሰረት ቀሪውን 63 ሺህ 970 ሄክታር መሬት በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ተሰብስቦ እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል፡፡
በዞኑ በመኸር ምርት ዘመኑ በተለያየ ሰብል ከለማው መሬት ከ13 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ በተደረገው የቅድመ ምርት ግምገማ መተንበዩን ተናግረዋል።
በዞኑ ግንባር ቀደም አርሶ አደር የሆኑት አስፋው ለታ በልማት ቡድን በመደራጀትና ተማሪዎችን በማሳተፍ የደረሱ ሰብሎች መሰብሰባቸውን ገልጸዋል።
እሳቸውም በ10 ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን የበቆሎ፣ የጤፍና የበርበሬ ሰብል ሰብሰብው ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
በወረዳው የጨሪ ጃርሶ ቀበሌ አርሶ አደር አቢቲ ደረጀ በበኩላቸው በአምስት ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን በቆሎና ጤፍን ጨምሮ ሌሎች የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ መሰብሰባቸውን አመልክተዋል፡፡