በክልሉ የችግኞችን የመፅደቅ ምጣኔ 80 በመቶ ለማድረስ አየተሰራ ነው

81
ባህር ዳር መስከረም 22/2011 በአማራ ክልል በክረምት ወቅት የተተከሉ ችግኞችን የፅድቀት ምጣኔ 80 በመቶ ለማድረስ የእንክብካቤና ጥበቃ ሥራ እያከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። በቢሮው የሥነ-ህይወታዊ ጥበቃና የጥምር ግብርና ባለሙያ አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለጹት በክረምት ወቅት በኅብረተሰቡ ተሳትፎ 1 ቢሊዮን 722 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል። ችግኞቹ በ368 ሺህ 590 ሄክታር የአፈርና ውሃ ጥበቃ በተከናወነባቸውና በደን ክልሎች እንዲሁም በግልና በወል መሬት ላይ መተከላቸውን ተናግረዋል ። “የተተከሉ ችግኞችን የመፅደቅ መጣኔ 80 በመቶ ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ ነው” ያሉት ባለሙያው፣ ችግኞቹን የማረም፣ የመኮትኮትና ከእንስሳት ንክኪ የመጠበቅ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል። ቢሮው 198 ሺህ ለሚሆኑ የተፋሰስ ኮሚቴ አባል አርሶ አደሮች በችግኝ ተከላና እንክብካቤ ግንዛቤ እንዲያገኙ መደረጉን ባለሙያው አስታውቀዋል። በምዕራብ ጎጃም ዞን በዞኑ ሰከላ ወረዳ የኮለል ለቻ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ስሜነህ ሞላልኝ በሰጡት አስተያየት በክረምቱ ወራት ከግማሽ ሄክታር በሚበልጥ የተራቆተ መሬት ላይ 10 ሺህ የደን ችግኞችን ተተክለዋል። ችግኞቹን በመኮትኮትና ውሃ በማጠጣት እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። “ችግኝ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በተግባር እየተረዳን በመምጣታችን የደን ችግኝ በተተከለባቸውና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ የተከናወነባቸውን ተፋሰሶች ከእንስሳት ንክኪ እየጠበቅን ነው” ብለዋል። “በተከለሉ ተፋሰሶች እንስሳት ለቆ የተገኘ አርሶ አደር በአንድ ከብት 50 ብር መቀጫ እንዲከፍል ተስማምተን ተግባራዊ እያደረግን ነው” ሲሉም ተናግረዋል ። በሩብ ሄክታር ለምነቱን ባጣ መሬታቸው ላይ የተከሏቸውን ችግኞች እየተንከባከቡ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ  በወረዳው የአባይ ሳንግብ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ወንድም ተሻለ ናቸው። ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ባለፈው ዓመት ከተተከሉ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ 63 ነጥብ 9 በመቶዎቹ ፀድቀዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም