የደቡብ ክልል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በሕገ ወጥ መንገድ የተወረረ ከ278 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የከተማ መሬት ማስመለሱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ክልል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በሕገ ወጥ መንገድ የተወረረ ከ278 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የከተማ መሬት ማስመለሱን ገለጸ
ሐዋሳ (ኢዜአ) ታህሳስ 27/2015 ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ባከናወናቸው ተግባራት በሕገ ወጥ መንገድ የተወረረ ከ278 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የሆነ የከተማ መሬት ማስመለሱን የደቡብ ክልል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ፋሲካ ጌታቸው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሌብነትና ሙስና ተግባራትን ለመከላከል እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
የሙስና ተግባር በተለያየ መንገድ እየተፈጸመ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በተለይ በሕገ ወጥ መሬት ወረራ፣ በጨረታና በቅጥር ዙሪያ የሚፈፀሙ የሙስና ተግባራትን በተመለከተ በርካታ ጥቆማዎች ከህብረተሰቡ ለኮሚሽኑ እየደረሰ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ጥቆማዎችን መሠረት በማድረግ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው፤ ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ላይ ባከናወናቸው የክትትል ስራዎች ከ278 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የተወረረ የከተማ መሬት ማስመለስ ችለናል ብለዋል፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት ከጨረታና ሌሎች ሂደቶች ጋር ተያይዞ ያለአግባብ የተከፈለና ለክፍያ የተዘጋጀ 378 ሚሊዮን ብር ማስመለስ ችለናል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በዚህ ዓመት የመጀመሪዎቹ ሶስት ወራት ደግሞ ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ እንዲመለስ መደረጉን ነው የጠቆሙት፡፡
በዚህም ያለአግባብ ሊባክን የነበረ የመንግስትና የህዝብ ሀብት ማዳን መቻሉን ጠቁመው፤ ኮሚሽኑ የተሰጠውን አደራ ለመወጣት ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉን አመላክተዋል፡፡
በተቋማት ውስጥ በተለያየ የሥራ ድርሻና ኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ግለሰቦችን ሀብት የመመዝገብና ትክክለኛነቱን የማረጋገጥ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነም አመልክተዋል።
የሙስና፣ ብልሹ አሰራርና የሀብት ብክነትን ለመከላከል ጥናት በማካሄድና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የማመላከት ሥራም እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
ጥናቱ ከተደረገባቸው መስሪያ ቤቶች ጋር ውጤቱን በተመለከተ በግልጽ ውይይት መደረጉን የጠቆሙት አቶ ፋሲካ፤ የተግባቡባቸው የመፍትሔ ሀሳቦችና የአተገባበር ሂደታቸውን የመከታተል ሥራ በኮሚሽኑ በኩል እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
ኮሚሽኑ በዋናነት ሙስናን መከላከል ላይ ያተኮረ ሥራ እንደሚያከናውን ጠቅሰው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ብሔራዊ የፀረ-ሙስና ግብረ-ኃይል በህብረተሰቡ ዘንድ ሙስናን መከላከልና መቆጣጠር ላይ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩን ተናግረዋል።