የምርት ጥራት ጉድለት የተገኘባቸው ከ381 ቶን በላይ የተለያዩ የምግብ ምርቶች ተወገዱ

178

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 27/2015 የምርት ጥራት ጉድለት የተገኘባቸውና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ከ381 ቶን በላይ የተለያዩ የምግብ ምርቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማድረጉን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ያለፉትን ስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጻም አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አበራ ደነቀ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ባለፋት ስድስት ወራት በተደረገ ክትትልና ቁጥጥር ከ381 ቶን በላይ የተለያዩ የምግብ ምርቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ተደርጓል።

ምርቶቹ ገበያ ላይ እንዳይውሉ የተደረገው የምርት ጥራት ጉድለት ስለተገኘባቸውና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው በማለፋ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ከተደረጉት የምግብ ምርቶች መካከል ዘይቶች፣ የተለያዩ የታሸጉ ውሃዎች፣ የቢራ ገብስ፣ የተለያዩ ጁሶችና በርካታ ምግቦችና መጠጦች ይገኙባቸዋል ብለዋል።

እንዲሁም ግምታቸው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ መድኃኒቶችና የመድኃኒት ግብአቶች ገበያ ላይ እንዳይውሉ መደረጉንም ጠቁመዋል።

ከ98 ሺህ በላይ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችንና የውበት መጠበቂያ ቁሳቁሶች ደረጃቸውን ሳይጠብቁ በመመረታቸው ተወግደዋል።

ባለስልጣኑ ባደረገው ክትትል ከ200 በሚበልጡ መዝገቦች ላይ ክስ የመሰረተ ሲሆን፤ በ71 መዝገቦች ላይ ከአምስት ሺህ ብር ጀምሮ እስከ 10 ዓመት የሚደርሱ ቅጣቶች ማስጣሉንም አብራርተዋል።

ባለስልጣኑ ከህዝብ በተሰጠው ጥቆማ 378 ባለ ሀያ ሊትር ጀሪካን ዘይት በመክፈት በህገ-ወጥ መንገድ ከሌላ ምርት ጋር በመቀላቀል ሊሸጡ የሞከሩ ግለሰቦችን በመያዝ ጉዳዩ በፖሊስ እንዲመረመር እያደረገ እንደሚገኝም አቶ አበራ አስረድተዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ በተለይ በዓልን አስታከው ሊመጡ የሚችሉ የማጭበርበር ስራዎችን ከባለስልጣኑና ከፍትህ አካላት ጋር በመተባበር ለህግ እንዲቀርቡ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም