ቀጥታ፡

በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ከ360 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ወደ ትግራይ ክልል ተጓጉዟል

አዲስ አበባ ታህሳስ 27 ቀን 2015 (ኢዜአ) በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ360 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ወደ ትግራይ ክልል መጓጓዙን የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታወቀ።

መንግሥት በክልሉ የነዳጅ አቅርቦቱ እንዳይስተጓጎል ግብረ-ኃይል አቋቁሞ እየሠራ መሆኑም ተጠቁሟል።

በመንግሥትና በህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በርካታ የአገልግሎት መስጪያ ተቋማት ዳግም ሥራ መጀመራቸው ይታወቃል፡፡

ለአብነትም ባንክ፣ ቴሌኮም፣ የአውሮፕላን ትራንስፖርት እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዳግም ሥራ የጀመሩ ሲሆን፤ ሰብዓዊ ድጋፍም በስፋት እየቀረበ ነው፡፡

በትግራይ ክልል የነዳጅ አቅርቦትን በተሳለጠ ሁኔታ ለማከናወን ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱም ተገልጿል፡

የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሰሃረላ አብዱላሂ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ መንግሥት ግብረ-ኃይል በማቋቋም ነዳጅ ያለምንም መስተጓጎል ከጂቡቲ ወደ ክልሉ በቀጥታ እንዲገባ እየተደረገ ነው፡፡

ድርጅቱ ከታኅሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ክልሉ ነዳጅ እንዲጓጓዝ  ለነዳጅ አቅራቢዎች ፈቃድ መስጠቱን ያስታወሱት ኃላፊዋ፤ ይህን ተከትሎም  ባለፈው አንድ ሳምንት በስምንት የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከ360 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ወደ ትግራይ ክልል መጓጓዙን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በመቀሌ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች በጦርነቱ ጉዳት ያልደረሰባቸው በመሆኑ፤ ከማደያዎቹ ባለቤቶችና ኩባንያዎች ጋር በመነጋገር  ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

በተጨማሪ  የነዳጅ አቅርቦቱ በሁሉም የክልሉ ከተሞች እንዲዳረስ እየተሠራ መሆኑንም ነው የጠቀሱት፡፡

በአጠቃላይ መንግስት እያከናወነው ያለው ሥራ የነዳጅ አቅርቦቱን ተደራሽ በማድረግ ረገድ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደትም ከመቀሌ እስከ ዛልአንበሳ ያሉ ቶታል፣ ኖክ፣ ታፍና ኦይል ሊቢያ ማደያዎች የነዳጅ ጭነት ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
 
በክልሉ ለሁለት ዓመታት ያህል የነዳጅ ማደያዎች ተዘግተው የቆዩ በመሆኑ ''እንዲያውቁት'' በሚል አሁን ያለውን ሀገራዊ የነዳጅ የመሸጫ ዋጋ ዝርዝር መላኩንም ጠቁመዋል።
 
በቅርቡም ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትና ኩባንያዎች የተውጣጡ አባላት ወደ ክልሉ በመጓዝ የነዳጅ አጠቃቀም እንቅስቃሴ ምልከታ ያደርጋል ብለዋል።

በቀጣይም በክልሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የታለመ የነዳጅ አቅርቦት ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም