አምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ በውጭ ንግድ ቀረጥ ማበረታቻ ስርዓት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ነው--የጉምሩክ ኮሚሽን

አዲስ አበባ ታህሳስ 27/2015 (ኢዜአ) የወጭ ንግድ ቀረጥ ማበረታቻ ስርዓት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩትን ችግሮች በመፍታት ሀገር ከወጭ ንግድ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ የወጭ ንግድ ቀረጥ ማበረታቻ ስርዓት አልግሎት አሰጣጥ ላይ በተመዘገቡ ውጤቶችና ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

በኮሚሽኑ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አዘዘው ጫኔ፤ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት መንግስት የአምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ የወጭ ንግድ ቀረጥ ማበረታቻ ስርዓትን መዘርጋቱን ጠቅሰው ከዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሀገር የሚገባትን ገቢ እንድታገኝ ከጥገናዊ ለውጥ ባሻገር መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣትም በመንግስት ተቋማት መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ጠንካራ መሆን እንዳለበት አስረድተው ከወቅቱ ጋር የማይሄዱ የህግ ማእቀፎች እንደሚሻሻሉም አመላክተዋል።

የወጭ ንግድ ቀረጥ ማበረታቻ ላይ የተገኙ ውጤቶች እና የታዩ ውሱንነቶችን በተመለከተ በጉምሩክ ኮሚሽን የአምራች እና የወጭ ንግድ አሰራር እና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በወይዘሮ ገነት አብርሀም የመነሻ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ዳይሬክተሯ በሰነዱ ላይ እንዳመላከቱት የወጭ ንግድ ቀረጥ ማበረታቻ ስርዓት፤ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አምራች ድርጅቶች ወይም ግብዓት አቅራቢዎች ለምርት ግብዓት የሚውሉ ጥሬ ቃዎችን ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወይም ቅድሚያ ክፍያ በመፈጸም ወደ ሀገር የሚያስገቡበት ስርዓት ነው።

ይህ የወጭ ንግድ ቀረጥ ማበረታቻ ስርዓት ዋና ዓላማ የኢኮኖሚ ልማትን ለማፋጠን፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማጎልበት፣ የካፒታል ፍሰትን ለማሳደግ ለዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እና ሀገራዊ ምርቶችን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ መሆኑንም ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።

የወጭ ንግድ ቀረጥ ማበረታቻ ስርዓት አዋጅ እና መመሪያ ወቅቱን የዋጁ አለመሆናቸውንና ስርዓቱ ቀላል ግልጽ እና ለቁጥጥር ምቹ አለመሆኑን በችግርነት ተነስተዋል።

በተቋማት መካካል ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ደካማ መሆኑም ከዘርፉ የሚጠበቀው ውጤት እንዳይመጣ ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውን ትላንት በተካሔደው ውይይት ላይ በተሳታፊዎች ከተነሱት መካከል እንደሚገኙበት ከኮሚሽኑ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም