በደቡብ ክልል የትምህርት ግብዐት ግዢና አስተዳደር ስርአት ለሙስናና ብልሹ አሰራር የተጋለጠ ነው

50

ሀዋሳ (ኢዜአ)ታህሳስ 26/2015  በደቡብ ክልል የትምህርት ግብዐት ግዢና አስተዳደር ስርአት ለሙስናና ብልሹ አሰራር ተጋላጭ መሆኑን በጥናት ማረጋገጡን የክልሉ ሥነ ምግባርና ጸረሙስና ኮሚሽን አስታወቀ ፡፡

የደቡብ ክልል ሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በክልሉ ትምህርት ሴክተር የግብዐት ግዢና አስተዳደር አሰራር ለሙስናና ብልሹ አሰራር ያለውን ተጋላጭነት በተመለከተ ባጠናው ጥናት ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት የፓናል ውይይት በዲላ ከተማ ተካሂዷል ፡፡

የፓናል ውይይቱን የመሩት የክልሉ ሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበራ ኪጴ እንዳስታወቁት በኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ወስጥ ጉልህ ሚና ሊጫወት የሚችለውን የትምህርት ሴክተር ከሙስናና ብልሹ አሰራር የፀዳ ማድረግ ቁልፍ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡

ኮሚሽነሩ ለመማር ማስተማር ሂደቱ ጥራትና ተደራሽነት አስፈላጊ የሆኑ ግብዐቶች ሀገሪቱ ካላት ውስን ሀብት ላይ አልያም ከለጋሽ ሀገራት በሚገኝ ድጋፍ እንደሚሟሉ ጠቅሰዋል ፡፡

እነዚህን ውስን ሀብቶች ከሌብነት በፀዳ መልኩ ለታለመለት ዓላማ ማዋል አለመቻል መሰረታዊ ችግር መሆኑን ያስረዱት አቶ አበራ የትምህርት ሴክተሩ የግብዐት ግዢና አስተዳደር ሂደትም ለሙስናና ብልሹ አሰራር የተጋለጠ መሆኑን ኮሚሽኑ ባስጠናው ጥናት መረጋገጡን ጠቁመዋል ፡፡

አቶ አበራ አክለው መሰል ክፍተቶችን ለመሙላት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል ፡፡

በኮሚሽኑ የሙስና መከላለከል ጥናት አማካሪ አቶ ብርሀኑ ሶላሞ ጥናቱ በክልሉ ትምህርት ሴክተር የግብዓት አቅርቦትና ሥርጭት ላይ ያተኮረ እንደሆነ ጠቁመዋል።

"በተለይም ከግዢ ጥናት ጀምሮ ወደ ተቋማት እስከማሰራጨት ድረስ ያለው አሰራር ለሙስናና ብልሹ አሰራር የተጋለጠና ተጠያቂነት ያልሰፈነበት መሆኑን ያመላከተ ነው" ብለዋል ፡፡

በተለይ በትምህርት ቤቶች ደረጃ የግዢ ዕቅድ ዝግጅትና አፈፃፀም አለመከተልና ግንዛቤ አለመኖር፣ በግልፅ ጨረታ ግዢ አለመፈፀምና ከአንድ ተቋም ተደጋጋሚ ግዢ መፈፀም እንዲሁም ያለ ማረጋገጫ ርክክብ ማድረግና መሰል ግድፈቶች እንደሚስተዋሉ አብራርተዋል ፡፡

ለተማሪዎች ምገባ የሚውሉ እህልና የምግብ ቁሳቁሶችም እንዲሁ ጥራታቸውን ካለመጠበቅ ባለፈ በጊዜው ጥቅም ላይ ባለማዋል መጋዘን ውስጥ ባክነው የሚቀሩበት አጋጣሚ እንዳለ በተደረገው ጥናት እንደተደረሰበት አስረድተዋል ፡፡

ከክልል ጀምሮ የሚመለከታቸው አካላት ተናበውና የጋራ ዕቅድ አውጥተው አለመስራታቸውም ክፍተቱን እንዳሰፋው ጠቁመዋል ፡፡

This image has an empty alt attribute; its file name is 3-1.png

ኮሚሽኑ ከትምህርት ሴክተሩ እና ሌሎች ጥናት የሚደረግባቸው ተቋማት ጋር ባለው የመግባቢያ ሰነድ መሰረት ለሌብነትና ሀብት ብክነት ተጋላጭ የሚያደርጉ የአሰራር ክፍተቶችን ለመሙላት በጥናት ላይ የተመሰረተ ምክረ ሀሳብ የማቅረብ ሥራ እንደሚሰራ አስረድተዋል ፡፡

ከዚህ ባሻገር በቂ ክትትል በማድረግና በኦዲት ግኝቶች ላይ በመመስረት የተጠያቂነት ሥርዐት መዘርጋትና የሀብት ማስመለስ ሥራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ አስታውቀዋል ፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ  የሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ዳይሬክተር አቶ ወርቅአገኘሁ አሻግሬ "ኮሚሽኑ ያካሄደው ጥናት በሴክተሩ ውስጥ ያሉ የአሰራር ክፍተቶችና የመፍትሔ ሀሳቦችን በግልፅ ያስቀመጠ ነው" ብለዋል፡፡

"ጥናቱ ጉድለቶችን አርሞ ከሙስናና ብልሹ አሰራር የፀዳ ተግባር ለመፈፀምና የተፈጠረውንም ለማረም ትልቅ እገዛ ያደርግልናል" ሲሉም አክለዋል፡፡

በሴክተር ደረጃ ከሌብነት የፀዳና ግልጸኝነት የሰፈነበት አሰራር ለመዘርጋት ሥልጠና ከመስጠት ጀምሮ ለሌብነት የተጋለጡ የግዢ ጨረታዎችን እስከመሰረዝ ድረስ የተቀናጀ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል ፡፡

የኦዲት ግኝቶችን መሰረት በማድረግም የእርምትና ክፍተቶችን የመሙላት ሥራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት  እየተሰራ መሆኑን  ጠቁመዋል ፡፡

አቶ ወርቅአገኘሁ አክለው ከኮሚሽኑ ብሎም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የሴክተሩ የግብዐት ግዢ፣ አቅርቦትና ስርጭት የሕግ ማዕቀፎችና መመሪያዎችን ብቻ የተከተለ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ሥርዐተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ በጎነህ ለማ ለሌብነት ተጋላጭ የሆኑ የአሰራር ክፍተቶች በአብዛኛው በትምህርት ቤቶች ደረጃ እንደሚስተዋሉ ገልፀዋል ፡፡

በተለይ የኦዲትና የንብረት ቆጠራ ሥርዐቶች በትምህርት ቤቶች ያልተለመደ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

አንዳንዴም ርዕሳነ መምህራን ያለ ግዢ ኮሚቴ ውሳኔ በራሳቸው መንገድ ግዢ የሚፈፅሙበት አጋጣሚም እንደሚፈጠር ጠቅሰዋል ፡፡

መምሪያው የሚደርሱትን ጥቆማዎች መሠረት አድርጎ ከሚወስዳቸው የማስተካከያ እርምጃዎች ባሻገርም ተጋላጭነትን የሚቀንሱ አሰራሮችን ለመዘርጋት እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል ፡፡

በተለይ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የራሳቸው የሆነ የፋይናንስ አስተዳደር እንዲፈጠር በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል ፡፡

በውይይቱ ላይ ከኮሚሽኑ፣ ከትምህርት ቢሮው እንዲሁም ዞንና ወረዳን ጨምሮ የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም