በበዓል ወቅት የመብራት መቆራረጥና የውሃ ችግር እንዳያጋጥም የተቀናጀ ግብረ ኃይል ተቋቁሟአል - ኢዜአ አማርኛ
በበዓል ወቅት የመብራት መቆራረጥና የውሃ ችግር እንዳያጋጥም የተቀናጀ ግብረ ኃይል ተቋቁሟአል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 26/2015 በአዲስ አበባ በበዓል የመብራት መቆራረጥና የውሃ ችግር እንዳያጋጥም የተቀናጀ ግብረ- ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን የከተማ አስተዳደሩ ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ታረቀኝ ወርቅነህ በሰጡት መግለጫ፤ የፊታችን ቅዳሜ ለሚከበረው የገና በዓል የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተሳለጠ አገልግሎት ለነዋሪው ለማቅረብ ዝግጅት አጠናቀዋል ብለዋል።
በተለይም የመብራት መቆራረጥና የውሃ ችግር እንዳያጋጥም ከወዲሁ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፤ የተቀናጀ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
የእነዚህ አገልግሎቶች ችግር ቢያጋጥምም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ሕብረተሰቡ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበው፤ አደጋ ቢያጋጥም እንኳን የእሳትና ድንገተኛ አደጋ በዋናው መሥሪያ ቤቱና በዘጠኙም ቅርንጫፎቹ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅትም ለበዓሉ ጤናማ የሆነ ሥጋ ለማቅረብ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት፡፡
ሕብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር የራስና የአካባቢን ንጽህና በመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣም አስገንዝበዋል።