ቀጥታ፡

ሀገሬው በዓል በዘዴ ቢያከብርስ?

ታህሳስ (ኢዜአ) 26/2015 በርግጥ ኅይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት ለኢትዮጵያዊያን እሴቶች መሆናቸው ዕሙን ነው።

በዓላት የወዳጅ ዘመድ እና ጎረቤታሞች መፈቃቀድ፣ መተሳሰብ፣ አብሮነት እና የደስታ ቱርፋቶች አሏቸው።

በብዙሃኑ ኢትዮጵያዊያን ክብረ በዓላት በጉጉት ይናፈቃሉ፤ የክት አልባሳት እና ምግብና መጠጦች በገፍ ይሸመታሉ፤ የቤትና የግል መዋቢያ ምርቶችን በሰፊው ይገበያሉ።

በዚህ ሂደት "ከእጅ ወደ አፍ" በሆነ ገቢ ባለው ብዙሃኑ ማህበረሰብ ዘንድ ከዘወትራዊ ወጭዎች በተለዬ በዓል ድል አድርጎ በማክበር ጉጉት እና የማድረግ አቅም ሲጋጩ ማስተዋል የተለመደ ነው።

በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የልማት ኢኮኖሚክስ ተመራማሪ ዶክተር ተስፋዬ ጮፈና እንደሚሉት የበዓላት ወጭዎች እና ምጣኔ ሀብታዊ አቅም ሊመጣጠኑ ግድ ይላል።

በሰዋዊ ባህሪ ለሚፈለገው ጉዳይ መስዕዋትነት መክፈል ግድ ቢልም ምጣኔ ሀብታዊ ጽንሰ ሀሳብ ግን የበዓላት ወቅት የሸማች አላስፈላጊ ወጪዎች በአመክንዮዊ ግብይት ካልተመራ መዘዙ የከፋ ነው ባይ ናቸው።

ኢትዮጵያዊያን በበዓላት ጊዜ 'በደስታ መሻትም ይሁን በአቻ ግፊት' ላልታሰቡ ወጪዎች እና ብድር ከመዳረግ፣ በኑሮ ጫና ከመሳቀቅ፤ 'በዓላትን በዘዴ በድምቀት ማክበር ቢለመድስ" ሲሉ ይመክራሉ።

በዓልን በማክበር ፍላጎትና አቅም ጋር ለማጣጣምም ሁነኛ ዘዴም፤ 'እንደ ቤቴ እንጂ እንደ ጎረቤቴ አላድርም' በሚለው ብሂል አቅምን ባገናዘበ እና የህሊና ነጻነት ባጎናጸፈ አግባብ ማክበር ይገባል ይላሉ የምጣኔ ሃብት ምሁሩ።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያዊያን ደካማ የቁጠባ ባህል መኖር ለበዓላት አላስፈላጊ ወጪዎችን ተከትሎ ለሚከሰቱ የኑሮ ጫናዎች የራሱ አሉታ እንዳለው ይገልጻሉ።

የቁጠባ ባህል ለግለሰብና ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ ቁጠባን መለማመድ መሰል ሁነቶችን ለጭንቀት ሳይዳረጉ፣ በዓልን በቅጡ ለማስተናገድና የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ያግዛል።

እናም ዜጎች የቁጠባ ባህልን ማጎልበትና ገቢን በመጨመር ኑሮን በዘዴ ለመኖር፣ በዓልን በልኩ ለማክበር ይበጃል ባይ ናቸው።

በመሆኑም አቅምን ባገናዘበ እና የህሊና ነጻነት ባጎናጸፈ አግባብ ለማክበር "ሀገሬው በዓል በዘዴ ቢያከብርስ? የሚል ጥያቄ እናነሳለን።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም