የትግራይን ክልል ለማረጋጋትና መልሶ ለማቋቋም አስተዋጽኦ ላበረከቱ አመራሮች የእውቅናና ምስጋና መርሃ ግብር ተከናወነ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይን ክልል ለማረጋጋትና መልሶ ለማቋቋም አስተዋጽኦ ላበረከቱ አመራሮች የእውቅናና ምስጋና መርሃ ግብር ተከናወነ
አዲስ አበባ(ኢዜአ) ታህሳስ 26/2015/ በትግራይ ክልል ህዝቡን በማረጋጋትና የመሰረተ ልማት ተቋማትን መልሶ በመገንባት አገልግሎት ለማስጀመር ሲሰሩ ለነበሩ አመራሮች የእውቅናና ምስጋና መርሃ ግብር ተካሄደ፡፡
መርሃ ግብሩ "ሰላም የማይታጠፍ የብልጽግና አቋም" በሚል ርእስ ነው የተካሄደው፡፡
በኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ግጭት ተከትሎ መንግስት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የአመራር ስምሪት በመስጠት መረጋጋት እንዲፈጠርና መሰረተ ልማቶች መልሰው እንዲገነቡ ሲያደረግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ለትግራይ ክልል ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም መልሶ ግንባታ የአመራርና ባለሙያ ስምሪት ተደርጎ የሰብዓዊ አቅርቦት፣ ተፈናቃዮችን የመመለስ፣ መሰረተ ልማት የመገንባትና አገልግሎቶችን መልሶ የማስጀመር ስራ ተከናውኗል፡፡
በዚህም በችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያገኙ፤ እንደ መብራት፣ መንገድ፣ ቴሌኮሙኒኬሽና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ጥገና ተደርጎላቸው ዳግም አገልግሎት እንዲጀምሩ ላደረጉ አካላት እውቅና ተሰጥቷል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ግጭት በነበረበት ወቅት የትግራይን ህዝብ ችግር ለመፍታት ቁርጠኛ በመሆን ወደ ስፍራው ያቀኑ አመራሮች የኢትዮጵያ ጀግኖች ናቸው፡፡
አመራሮቹ መንግስትና ብልጽግና ፓርቲ የጣለባቸውን ሃላፊነት በመቀበል ለመንግስትና ለትግራይ ህዝብ የመፍትሔ አካል በመሆን አኩሪ ታሪክ ፈጽመዋል ብለዋል፡፡
የአመራር ስምሪት የተሰጠው በተለይ የትግራይ ህዝብ የመንግስትን ድጋፍ በሚሻበት ወቅት እንደነበር የገለጹት ምክትል ፕሬዘዳንቱ፤ ህዝቡ ሰብዓዊ እርዳታ፣ የመሰረተ ልማትና ህዝባዊ አገልግሎት እንዲያገኝ አድርገዋል ብለዋል፡፡
በመሆኑም የትግራይን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ አኩሪ ተግባር መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህን አገርና ህዝብን የሚያኮራ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ብርቅዬ አመራሮች ላቅ ያለ ምስጋና ማቅረብ ይገባል ብለዋል፡፡
የትግራይን ክልል በማረጋጋትና መልሶ በማቋቋም ሲያስተባበሩ የነበሩት አቶ በዙ ዋቅቤካና አቶ አዝመራ አንዴሞ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በመወጣት ህዝቡ በመንግስት ለይ የነበረውን እምነት ከፍ እንዲል ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በመጀመሪያዎቹ ቀናት በህዝቡ ዘንድ ፍርሃትና ስጋት ይስተዋል እንደነበር የገለጹት አስተባባሪዎቹ፤ በሂደት በመንግስት ላይ ያለው እምነት እየጎለበት በሰላምና መረጋጋት እንዲሁም በመልሶ ግንባታ ከጎናችን ተሰልፏል ብለዋል፡፡
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የተረጋጋና ህዝቡም መደበኛ ህይወት የጀመረበት አውድ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡