ቀጥታ፡

በአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ለረዥም ጊዜ አብሮ የቆየ መሆኑ የተሻለ ጉዞ ለማድረግ ያግዘዋል-ተጫዋቾች

 አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታኅሳስ 26 ቀን 2015 የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ወይም  በቻን የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ለረዥም ጊዜ አብሮ የቆየ መሆኑ የተሻለ ጉዞ ለማድረግ እንደሚያግዘው ኢዜአ ያነጋገራቸው ተጫዋቾች ተናገሩ፡፡

ተጫዋቾቹ ይህን የተናገሩት በአልጀሪያ አዘጋጅነት በሚከናወነው ስድስተኛው የቻን ውድድር ለመሳተፍ ከመጓዛቸው በፊት የመጨረሻ ልምምዳቸውን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ላይ ባከናወኑበት ወቅት ነው።

የአገር ውስጥ ሊግ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ወይም ቻን ለወጣት ተጫዋቾች የፕሮፌሽናል ዕድልን የሚያስገኝ በመሆኑ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ተጫዋቾች ይናገራሉ፡፡

የቡድኑ የተከላካይ መስመር ተጫዋች አስቻለው ታመነና የአማካይ ሥፍራ ተጫዋቹ መስኡድ መሐመድ ለኢዜአ እንደገለፁት ለቡድን ውጤታማነት ለረዥም ጊዜ አብሮ መጫወት ከፍተኛ አስተዋጵኦ አለው ።

በቻን የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ለረዥም ጊዜ አብረው የተጫወቱ ተሰላፊዎችን ማሰባሰቡ በውድድሩ ለሚያደርገው ጉዞ እንደሚረዳው ገልፀዋል።                                 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተደለደለበት ምድብ ቀላል አለመሆኑን የገለጹት ተጫዋቾቹ የሚችሉትን አድርገው ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በተለይ ከውድድሩ በፊት ከሞሮኮ ጋር የሚያደርጉት ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለቅድመ ዝግጅታቸው እንደሚረዳቸው በመናገር መሰል የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች በፌዴሬሽኑ በኩል መመቻቸቱም ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትናንትና ሌሊት ወደ ግብፅ በማምራት ካይሮ ከተማ የደረሰ ሲሆን በዛሬው ዕለት ሞሮኮ መድረሱን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ አንድ ከአዘጋጇ አልጀሪያ፣ሊቢያና ሞዛምቢክ ጋር መደለደሉ ይታወቃል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሞዛምቢክ ጋር የሚያደርግ ይሆናል፡፡

ሰባተኛው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከጥር 5 ቀን እስከ ጥር 25 ቀን 2015 በአልጀሪያ ይደረጋል፡፡                                                                                                                                                                                                                                                                                               

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም